
ባሕር ዳር: ሰኔ 17/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የወጣቶች የሥራ መድረክ በባሕር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።
“ብቃት የሥራ ላይ ልምምድ ፕሮጀክት” በባሕር ዳር ከተማ የ2015 ዓ.ም የሥራ ላይ ልምምድ አፈጻጸም ማጠቃለያ እና የ2016 ዓ.ም የትግበራ ማስጀመሪያ የንቅናቄ መድረክ ተጀምሯል።
ፕሮጀክቱ በከተሞች የሥራ እድል ፈጠራ እና የምግብ ዋስትና ፕሮግራም ላይ የሚሠራ ሀገር አቀፍ ፕሮጀክት ነው።
የንድፍ ሃሳብ እና የተግባር እውቀትን በማቀናጀት የወጣቶችን እውቀትና ክህሎት በማሳደግ በርካቶች የሥራ እድል ተጠቃሚ የሚኾኑበትን እድል በመፍጠር በኩል በትኩረት እየሠራ ነው ተብሏል።
በንቅናቄ መድረኩ በተለያዩ በፕሮጀክቶችና የሥራ መስኮች የሰለጠኑ 1ሺህ 369 ወጣቶች የተግባር የሥራ ልምምድ ማስጀመሪያ ፕሮግራም ይፋ ይደረጋል ተብሏል።
በመድረኩ እንደተገለጸው ብቃት የሥራ ላይ ልምምድ ሀገር አቀፍ ፕሮጀክት በሚኖረው የሦስት ዓመት ቆይታ 78ሺህ ወጣቶችን የሥራ እድል ተጠቃሚ ለማድረግ አልሞ እየሠራ ነው ተብሏል።
በባሕር ዳር ከተማ ብቻ ደግሞ 4ሺህ 108 ወጣቶችን የሥራ እድል ተጠቃሚ ያደርጋል ነው የተባለው።
የአማራ ክልል ሥራና ሥልጠና ቢሮ ኀላፊ አረጋ ከበደ በመድረኩ እንዳሉት የሥራ አጥነት ችግር በአማራ ክልል አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል።
ምጣኔው ከሀገሪቱ የሥራ አጥነት ምጣኔ በላይ 20 በመቶ ነው ብለዋል። በቢሮው ከ1ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ሥራ ፈላጊዎች እንደተመዘገቡም ነው የተናገሩት።
“ሥራ አጥነት ባይተዋር የሚያደርገው ከሥራ ብቻ አይደለም ከማኀበራዊና ሰብዓዊ ልማትም ጭምር ነው” የሚሉት ኀላፊው ልዩ ትኩረት እንደሚያስፈልገውም አሳስበዋል።
ብቃት የወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ ፕሮጀክት ችግሩን ለማቃለል”ትልቅ የመጀመሪያ ነጥብ ነው” ብለውታል።
ፕሮጀክቱ የወጣቶችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ፣ ቀጣሪ ተቋማትንም ብቁ የሰው ኃይል እንዲያገኙ እድል የሚሰጥ ነው ብለዋል።
ኀላፊው ወጣቶች በሥራ ልምምድ ቆይታቸው ከፋብሪካዎቹ ጋር በሚኖራቸው ግንኙነት እውቀትና ክህሎታቸውን የሚያዳብሩበት እንዲኾንም አደራ ብለዋል።
ለፕሮጀክቱ ስኬታማነትም ሁሉም ባለድርሻ አካላት በኀላፊነት እንዲሰሩም ነው የተናገሩት።
ዘጋቢ ፦ ጋሻው አደመ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!