ሠላም፣ ፍቅር እና አንድነት እንዲሰፍን የበደልናቸውን ብቻ ሳይሆን የበደሉንንም ይቅር ማለት እንደሚገባ የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብፁዕ አቡነ አብርሃም አሳሰቡ።

433

ባሕር ዳር፡ ሕዳር 24/2012ዓ.ም (አብመድ) በባሕር ዳር ከተማ ለሦስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው ጸሎተ ምህላ ዛሬ ማምሻውን ተጠናቅቋል። የጥላቻ ዘመን አልፎ የፍቅር ዘመን እንዲመጣ ምዕመኑ በንፁህ ልቦናው መጾም እና መጸለይ እንደሚገባ ብፁዕ አቡነ አብርሃም ተናግረዋል።

“ከቂም እና በቀል ነፃ ከሆንን እግዚአብሔር ጸሎታችንን ይሰማል። ይቅር መባባልን ገንዘብ ማድረግ ይገባል እንጅ ጥላቻን፣ መለያዬትን፣ እገሌ ወገኔ ማለትን የክርስትና ሃይማኖት አስተምህሮ አይደለም። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ክርስትና ሃይማኖት ድንበር፣ ብሔር እና ቀለም አይለይም፤ ሁሉም ወገን እንደሆነ ቅዱስ መጽሐፍ ያስተምራል እንጅ” ብለዋል ብፁዕ አቡነ አብርሃም።

አንዱ አንዱን ሳይንቅ እና ሳያወግዝ በመማማር እና በመመካከር ለጋራ ቤት ለሆነችው ኢትዮጵያ መቆም እንደሚገባም ነው ብፁዕነታቸው የተናገሩት።

ፍቅርን፣ ሠላምን፣ መከባበርን፣ ይቅርባይነትን ከፈጣሪ አስተምሮ መማር እንደሚገባም አሳስበዋል።

በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሃይማኖት አባቶችና ምዕመናን ለሦስት ቀናት በመስቀል አደባባይ በጋራ ያካሄዱት ጸሎተ ምህላ ዛሬ ማምሻውን ተጠናቅቋል። የአደባባይ ጸሎተ ምሕላ ቢጠናቀቅም በየአድባራቱና ገዳማቱ የተጀመረው ጾም እስኪፈታ (እስከ ልደት በዓል) እንደሚቀጥልም ታውቋል።

ጸሎተ ምሕላው ሀገራዊ ሠላም፣ ፍቅር፣ አንድነትና መተዛዘን እንዲሰፍን ወደ ፈጣሪ የሚቀርብ ተማጽኖ እንደሆነ ታውቋል።

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

Previous articleበኩር ጋዜጣ ህዳር 22-2012 ዓ/ም ዕትም
Next articleሠላም፣ ፍቅር እና አንድነት እንዲሰፍን የበደልናቸውን ብቻ ሳይሆን የበደሉንንም ይቅር ማለት እንደሚገባ የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብፁዕ አቡነ አብርሃም አሳሰቡ።