ሠላም፣ ፍቅር እና አንድነት እንዲሰፍን የበደልናቸውን ብቻ ሳይሆን የበደሉንንም ይቅር ማለት እንደሚገባ የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብፁዕ አቡነ አብርሃም አሳሰቡ።

416

በባሕር ዳር ከተማ ለሦስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው ጸሎተ ምህላ ትናንት ማምሻውን ተጠናቅቋል። የጥላቻ ዘመን አልፎ የፍቅር ዘመን እንዲመጣ ምዕመኑ በንፁህ ልቦናው መጾም እና መጸለይ እንደሚገባ ብፁዕ አቡነ አብርሃም ተናግረዋል።

“ከቂም እና በቀል ነፃ ከሆንን እግዚአብሔር ጸሎታችንን ይሰማል። ይቅር መባባልን ገንዘብ ማድረግ ይገባል እንጅ ጥላቻን፣ መለያዬትን፣ እገሌ ወገኔ ማለትን የክርስትና ሃይማኖት አስተምህሮ አይደለም። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ክርስትና ሃይማኖት ድንበር፣ ብሔር እና ቀለም አይለይም፤ ሁሉም ወገን እንደሆነ ቅዱስ መጽሐፍ ያስተምራል እንጅ” ብለዋል ብፁዕ አቡነ አብርሃም።

አንዱ አንዱን ሳይንቅ እና ሳያወግዝ በመማማር እና በመመካከር ለጋራ ቤት ለሆነችው ኢትዮጵያ መቆም እንደሚገባም ነው ብፁዕነታቸው የተናገሩት።

ፍቅርን፣ ሠላምን፣ መከባበርን፣ ይቅርባይነትን ከፈጣሪ አስተምሮ መማር እንደሚገባም አሳስበዋል።

በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሃይማኖት አባቶችና ምዕመናን ለሦስት ቀናት በመስቀል አደባባይ በጋራ ያካሄዱት ጸሎተ ምህላ ትናንት ማምሻውን ተጠናቅቋል። የአደባባይ ጸሎተ ምሕላው ቢጠናቀቅም በየአድባራቱና ገዳማቱ የተጀመረው ጾም እስኪፈታ (እስከ ልደት በዓል) እንደሚቀጥልም ታውቋል።

ጸሎተ ምሕላው ሀገራዊ ሠላም፣ ፍቅር፣ አንድነትና መተዛዘን እንዲሰፍን ወደ ፈጣሪ የሚቀርብ ተማጽኖ እንደሆነ ታውቋል።

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

Previous articleሠላም፣ ፍቅር እና አንድነት እንዲሰፍን የበደልናቸውን ብቻ ሳይሆን የበደሉንንም ይቅር ማለት እንደሚገባ የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብፁዕ አቡነ አብርሃም አሳሰቡ።
Next article‹‹የሰፈር ኳስ መዘገብ አለበት!›› በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ሥነ ተግባቦት ትምህርት ክፍል መምህር እና ተመራማሪ