በስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ በ2014 ዓ.ም ከተተከሉ ችግኞች 88 በመቶውን ማጽደቅ እንደተቻለ የፓርኩ ጽሕፈት ቤት ገለጸ።

62

ባሕር ዳር: ሰኔ 16/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ጽሕፈት ቤቱ ከአፍሪካን ዋይልድ ላይፍ ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር የጸደቁ ችግኞችን ለባለድርሻ አካላት አስጎብኝቷል።

የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አዛናው ከፍያለው ጉብኝቱ በ2014 ዓ.ም በፓርኩ ውስጥ የተተከሉ ችግኞች ከፍተኛ የጽድቀት መጠን ሌሎች አካላትም ተሞክሮውን እንዲወስዱ ለማድረግ ያለመ ነው ብለዋል።

አቶ አዛናው በ2014 ዓ.ም በቅድመ ተከላና ድኅረ ተከላ ለችግኞች ጥንቃቄና እንክብካቤ መደረጉ እንዲኹም ችግኝ ተከላውን ከዘመቻ ማላቀቅ በመቻሉ ከተተከሉት ከ25 ሺህ በላይ ችግኞች ውስጥ 88 በመቶ የሚኾኑትን ማጽደቅ ተችሏል ብለዋል።

ለውጤታማነቱም የአፍሪካን ዋይልድ ላይፍ ፋውንዴሽን አስተዋጽኦ ከፍተኛ መኾኑንም ነው የገለጹት።

አቶ አዛናው አያይዘውም በተያዘው ዓመት በፓርኩ ውስጥ ከ30 ሺህ በላይ ሀገር በቀል ችግኞችን ለመትከል ከ 3 ነጥብ 3 ሄክታር በላይ የተከላ ቦታ ተለይቶ የጉድጓድ ቁፋሮ እየተከናወነ መኾኑንም ገልጸዋል።ከሐምሌ 5/2015 ዓ.ም ጀምሮ ተከላውን እንደሚጀምሩም አመላክተዋል።

የአፍሪካን ዋይልድ ላይፍ ፋውንዴሽን የሥነ ምሕዳር ባለሙያ በላይነህ አበበ ፋውንዴሽኑ ሰፊ የኾኑ የፓርክ ልማትና ጥበቃ ሥራዎችን እንደሚሠራ ገልጸዋል።

ከባለፈው ዓመት በፊት የተተከሉ ችግኞች የጽድቀት መጠን 19 ነጥብ 3 በመቶ እንደነበር አንስተው ፋውንዴሽኑ ዝቅተኛ የኾነበትን ምክንያት በመለየት ለማሻሻል ሠርቷል ብለዋል።

በቅድመ ችግኝ ተከላና ድኅረ ተከላ እንክብካቤ ማኅበረሰቡ ሙሉ ወጭ በመሸፈን ድጋፍ ማድረጉንም ነው የነገሩን። በዚህ ሂደት ፋውንዴሽኑ በ2014 ዓ.ም 480 እና በዚህ ዓመት ደግሞ ከ430 በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ ችሏልም ብለዋል።

በጉብኝቱ ተሳታፊዎች በፓርኩ ውስጥ የተመለከቱትና የጸደቀው ችግኝ በጥናትና በጥረት የመጣ ለውጥ በመኾኑ ልምድ የሚወሰድበት ነው ብለዋል።

ፓርኩ በተለያዩ ጫናዎች ውስጥ መኾኑን ታሳቢ ያደረገና ለአካባቢው ሥነ-ምሕዳር የሚስማሙ ብዛት ያላቸውን ችግኞች መትከል እንደሚያስፈልግም አስተያየት ሰጥተዋል።

ደባርቅ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ በጉብኝቱ የተሳተፉት አጋር አካላት የፓርኩን ደኅንነት ለመጠበቅ በተለይም በችግኝ ተከላ በጋራ እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል።

ዘጋቢ :- አድኖ ማርቆስ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleክልላዊ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ከፍተኛ የክልል እና የፌደራል የሥራ ኅላፊዎች በተገኙበት በደቡብ ጎንደር ዞን እየተካሄደ ነው።
Next articleፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለማስጀመር ሐዋሳ ገቡ።