
ባሕር ዳር: ሰኔ 16/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የትምህርት ጥራት ችግርና የፈተና አሰጣጡ በራሱ በተደጋጋሚ የስጋት ምንጭ መኾን ተዳምሮ በኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት ላይ ተግዳሮት ከኾነ ዓመታትን ተሻግሯል።
መንግሥት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ከትምህርት ሥርዓቱ እስከ የፈተና ሕግና ሥርዓትን እስከ ማስከበር የዘለቀ አሠራርን በቁርጠኝነት ማንበር ግድ እንደሚለው ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ መንግሥት ችግሩን ተረድቶ የትምህርት ጥራትን ለማምጣት ጥረት እያደረገ ስለመኾኑም አንዳንድ ተግባራቶቹ ያስረዳሉ።
ከእነዚህ ውስጥ ባሳለፍነው የትምህርት ዘመን የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ የሚወስዱ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ኩረጃን ለመከላከልና ሰላማዊ የፈተና ሁኔታን ለመፍጠር ሲባል በዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ እንዲፈተኑ መደረጋቸው የሚታወስ ነው።
በዚህ ዓመት የሚመረቁ የመንግሥትና የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎችም በሙሉ የመውጫ ፈተና እንዲወስዱ ለማድረግ በቂ ዝግጅት ማደረጉን ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል።
የመውጫ ፈተናው እንደ ሀገር የገጠመውን የትምህርት ጥራት ችግር ለመቅረፍ አንዱ የመፍትሔ አካል ተደርጎ ነው የሚወሰደው።
በትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ብቃትና ጥናት ማሻሻያ ዴስክ ኀላፊ ሰኢድ ሙሐመድ ለአሚኮ እንደተናገሩት ተመራቂ ተማሪዎች የመውጫ ፈተናውን እንዲወስዱ ለማድረግ በቂ ዝግጅት ተደርጓል።
በዚህ ዓመት የመውጫ ፈተናውን የሚወስዱ ተመራቂ ተማሪዎች ቁጥራቸው ወደ 170 ሺህ የሚጠጉ ናቸው ብለዋል ኀላፊው።
95 ሺህ ተመራቂ ተማሪዎች ከግል የትምህርት ተቋም ሲኾኑ 74 ሺህ 800 ተማሪዎች ደግሞ ከመንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ናቸው ብለዋል።
ለእነዚህ ተማሪዎች ታዲያ በ210 የቅድመ ምረቃ ፕሮግራሞች ነው የመውጫ ፈተና የተዘጋጀው ተብሏል።
ፈተናው የሚሰጠው በኦንላይን እንደኾነ የተናገሩት ኀላፊው ከሐምሌ 8/2015 ዓ.ም እስከ ሐምሌ 13 /2015 ዓ.ም ደግሞ ፈተናው የሚሰጥበት ቀን ነው ብለዋል።
የሁሉንም የትምህርት መስክ ያካተተ የመውጫ ፈተና እንደተዘጋጀም ነው የተገለጸው። ተመራቂ ተማሪዎች በተማሩበት የትምህርት መስክ ተገቢውን ዕውቀትና ክህሎት ይዘው እንዲወጡ ማድረግን ታላሚ ተደርጎ የተዘጋጀ ፈተና ስለመኾኑም ነው አቶ ሰኢድ የተናገሩት።
በእርግጥም የሀገሪቱ የትምህርት ጥራት ጉዳይ በቁርጠኝነት የመፍትሔ እርምጃዎችን የሚጠይቅ ጉዳይ ነው።
ለተጀማመሩ የተግባር ሙከራዎች ውጤታማነት ታዲያ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ትብብር የሚያሻ ይኾናል።
ዘጋቢ:-ጋሻው አደመ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!