የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን በአረንጓዴ አሻራ እንከላከል በሚል መሪ መልዕክት የፓናል ውይይት እየተካሄደ ነው።

35

አዲስ አበባ: ሰኔ 16/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን በአረንጓዴ አሻራ እንከላከል በሚል መሪ መልዕክት የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ጋር በመተባበር የፓናል ውይይት እየተካሄደ ነው።

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቋቋም በሚል የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር እየተገበረች ነው።

ባለፈው ዓመት 25 ቢሊዮን ችግኝ በመትከል በ2ኛው ዙር መርሐ ግብር ደግሞ 32 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ንቅናቄ ተጀምሯል።

ሁለቱ ተቋማት ባዘጋጁት የውይይት መድረክ ላይ የተገኙት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታዋ ወይዘሮ ሁሪያ አሊ ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚን ለመገንባትና የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ተጽዕኖን ለመከላከል የጀመረችው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ውጤት እያስገኘላት ነው ብለዋል። በተለይ በምግብ ራስን የመቻል ጥረት በመርሐ ግብሩ ታሳቢ ተደርጎ እየሠራ ያለ መኾኑን ገልጸዋል።

ወይዘሮ ሁሪያ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ሰፊ ድርሻ አላቸውና አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ዶክተር ማንደፍሮ ንጉሤ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የተለያዩ አሠራሮች እና ስትራቴጂዎችን ቀርጻ እየሠራች ነው ብለዋል።

የአየር ንብረት ለውጥን መከላከል ወይንም መቋቋም የምንችለው ሁላችንም በቅንጅት የድርሻችንን ስንወጣ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ የመገናኛ ብዙኃንና ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው ተቋማት የአየር ንብረት ለውጥን የምትቋቋም እና አረንጓዴ የኾነች ኢትዮጵያ ዕውን እንድትኾን የሚሠሩትን ሥራ አጠናክረው መቀጠል ይኖርባቸዋል ብለዋል።

በመድረኩ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ፣ የሰላም ሚኒስትሩ ብናልፍ አንዷለም እና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

በመድረኩ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ በቀጣናዊ ሰላምና ጸጥታ ፣ የአየር ንብረት ለውጥ እና የመገናኛ ብዙኃን ሚና በሚል ርእስ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት እየተደረገባቸው ነው።

ዘጋቢ፡- ድልነሳ መንግስቴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleፀደይ ባንክ ኢንተርፕራይዞችን በፋይናንስ እና በሥልጠና ለመደገፍ ከአሜሪካን ኮሌጅ ኦፍ ቴክኖሎጂ ጋር በጋራ እንደሚሠራ አስታወቀ።
Next article“170 ሺህ የሚጠጉ ተመራቂ ተማሪዎች የመውጫ ፈተናውን ይወስዳሉ” ትምህርት ሚኒስቴር