
ባሕር ዳር: ሰኔ 16/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ዞን ደራ ወረዳ ጎሃ ቀበሌ በተካሄደው አምስተኛው ክልል አቀፍ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ ተገኝተዋል። አረንጓዴ አሻራ የላቀ ሀገራዊ ፋይዳ እንዳለው ታምኖበት ሲጀመር ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ለተፈጻሚነቱ ከፍተኛ ርብርብ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
ይህም የአፈር መሸርሸርን በመቀነስ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል ብለዋል። የተራቆተው የሀገሪቱ የደን ሽፋን መጨመሩንም አንስተዋል።
ምክትል ፕሬዚዳንቱ ሀገር አቀፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ጠቃሚ መኾኑን በመረዳት ጠንክረው ለፈጸሙ አካላት ሁሉ ምሥጋና ይገባቸዋል ብለዋል። “አረንጓዴ አሻራችን ኢትዮጵያዊያን ለሀገር የሚጠቅም ሥራ ለመሥራት ቁርጠኛ መኾናችንን ያረጋገጥንበት ነው” ሲሉም ተናግረዋል።
መርሃ ግብሩ ላቅ ያለ ሀገራዊ ፋይዳን ይዞ የተጀመረ በመኾኑ ከዘርፉ ተጠቃሚ ለመኾን ሁሉም የላቀ እና ዘላቂ ርብርብ ማድረግ እንዳለበትም አሳስበዋል።
አቶ አደም አማራ ክልል በአረንጓዴ አሻራ ሥራዎች ከፍተኛ አፈጻጸም እንዳስመዘገበም ተናግረዋል። በቀጣይነትም በየተፋሰሱ ችግኞችን በመትከል እና በማጽደቅ ዘርፉን አማራጭ የሥራ አድል መፍጠሪያ ማድረግ እንደሚያስፈልግም መልዕክት አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!