“በአረንጓዴ አሻራችን ተጨባጭ ለውጥ የምናመጣው በተተከሉ ችግኞች የሕዝብ ተጠቃሚነት ሲረጋገጥ ነው” ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር)

68

ደብረ ታቦር: ሰኔ 16/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ በደቡብ ጎንደር ዞን ደራ ወረዳ ባዘጋጀው አምስተኛው የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ ላይ ተገኝተዋል።

ዶክተር ይልቃል ሀገራችን “ለምለሚቱ ኢትዮጵያ” እየተባለ የሚዘመርላት ቢኾንም የደን ሽፋኗ ተመናምኖ የአፈር መሸርሸር እየገጠማት ቆይታለች ብለዋል። ይህንን ሁኔታ በሕዝቦች ርብርብ ለመቀየር እና የአካባቢውን የአየር ሚዛን ለመጠበቅ ታስቦ ከአራት ዓመት በፊት የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ውጤት እያሳየ ስለመኾኑም ተናግረዋል። ዛፎችን በትጋት መትከል የከባቢ አየርን ሚዛን በመጠበቅ ድርቅን ይከላከላል፤ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥም ያስችላል ሲሉም ገልጸዋል።

ችግኞችን በቁጥር አብዝቶ ከመትከል በተጨማሪ በባለቤትነት በመንከባከብ ማጽደቅ እና ለውጤት ማብቃት እንደሚያስፈልግም አንስተዋል። ርእሰ መሥተዳድሩ “በአረንጓዴ አሻራችን ተጨባጭ ለውጥ የምናመጣው የተተከሉ ችግኞች ጸድቀው የሕዝብ ተጠቃሚነት ሲረጋገጥ ነው” ሲሉም ተናግረዋል። ችግኞችን ስንተክል አካባቢን መቀየር እና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ቁርጠኞች ኾነን እና ተማምነን መኾን አለበትም ብለዋል።

ችግኞችን ለመትከል የሚወጣው ጊዜ፣ ገንዘብ እና ጉልበት ከፍተኛ መኾኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት ከእንስሳት እና ከሰዎች ንክኪ ነጻ በማድረግ ማጽደቅ ያስፈልጋልም ብለዋል። በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የሚተከሉ ችግኞች ለምግብነት የሚውሉ እንዲኾኑ በትኩረት እየተሠራ ነው። በከተማም ይሁን በገጠር የማኅበረሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ በሚተከሉ ችግኞች የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ያስፈልጋል ሲሉ ርእሰ መሥተዳድሩ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በቀልን ለባለቤቱ እንተዋለን፣ እኛ ግን የእነርሱን ራዕይ እናስቀጥላለን” የእነ ዶክተር አምባቸው መኮንን ዘመዶች
Next article“አረንጓዴ አሻራችን ኢትዮጵያዊያን ለሀገር የሚጠቅም ሥራ ለመሥራት ቁርጠኛ መኾናችንን ያረጋገጥንበት ነው” የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ