
አዲስ አበባ: ሰኔ 15/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በሕዝብ የተጣለባቸውን ኃላፊነትና ተግባር በመወጣት ላይ እንዳሉ የተሠውት የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት የነበሩት ዶክተር አምባቸው መኮነን ፣ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና የፀጥታ ኃይሎች አራተኛ ዓመት የሰማዕትነት መታሠቢያ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
በዶክተር አምባቸው መኮነን ፋውንዴሽን አስተባባሪነት በተካሄደው መታሰቢያ መርኃ ግብር ላይ የተገኘችው የዶክተር አምባቸው መኮነን ልጅ መዐዛ መኮነን ይህ ፋውንዴሽን የተመሰረተበት ዋና ዓላማ ሀገርና ወገን በምክንያት እንዲያስብና የተሻለች ሀገር እንዲመሠረት በማሠብ ነው ብላለች። የዶክተር አምባቸው መኮነን ፋውንዴሽን ለስሙ ማስታወሻ ይኾን ዘንድ በትውልድ ግንባታ ላይ በርካታ ሥራ ይሠራል ስትል መዐዛ አምባቸው ተናግራለች። ፋውንዴሽኑ ባለቤትነቱ ሕዝብ ሲኾን የተቋቋመበትን ዓላማ ለማሳካት ሁሉም ሰው ሊረባረብ ይገባል ነው ያለችው።
ፋውንዴሽኑ እውን እንዲኾን ከፍተኛ ሥራ ከሠሩት መካከል ዶክተር እንዳለ ዳምጤ እንዳሉት ፋውንዴሽኑ በዶክተር አምባቸው ስም ቢሠየምም ሌሎቹም አመራሮች ይታወሱበታል ብለዋል። የዶክተር አምባቸው ፋውንዴሽን ትምህርት ላይ ትኩረት አድርጎ በመሥራት ስኮላርሽፖችን ከማመቻቸት ባሻገር በተለያዩ ክልሎች ቤተ መጽሐፍትን የመደገፍ፣ የማጠናከር፣ የጥናትና ምርምር ሥራ የመሥራት፣ በግብርና እና በአረንጓዴ ልማት ሥራዎች ጠንክሮ እየሠራ እንደኾነ ዶክተር እንዳለ ተናግረዋል።
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ኢንዱስትሪ ሚንስቴር ሚኒስትር መላኩ አለበል በበኩላቸው የሀገር ግንባታ እውን የሚኾነው ዜጎችን በማስተማር ነው ብለዋል፡፡ ሚኒስትሩ “ፋውንዴሽኑ ትምህርት ላይ በትኩረት ስለሚሠራ ፋውንዴሽኑን ለማገዝ ከፍተኛ ሥራ ይጠበቅብናል” ነው ያሉት፡፡ በመታሰቢያ ዝግጅቱ ላይ የፌደራልና የክልል ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።
ዘጋቢ፦ ሳሙኤል ኪሮስ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!