
ባሕር ዳር: ሰኔ 15/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ የኮሪያ ኤምባሲ አምባሳደር ኮንግ ሰኪሂ ከጎንደር ከተማ ከንቲባ ተወካይና በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የከተማ አሥተዳደሩ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ደብሬ የኃላ ጋር የኮሪያ መንግሥት በከተማዋ የልማት ሥራዎች ላይ በሚያግዝባቸው ሥራዎች ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡
በውይይቱ አምባሳደር ኮንግ ሰኪሂ ኮሪያና ኢትዮጵያ የ60 ዓመታት የዲፕሎማሲ የግንኙነት ታሪክ እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡ ኮሪያውያን በ1950ዎቹ ለነፃነታቸው በሚታገሉበት ወቅት ከ6 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን በተባበሩት መንግሥታት አማካኝነት ድጋፍ ማድረጋቸውን አስታውሰው ሀገራቸው አሁን ለደረሰችበት ዕድገት የኢትዮጵያውን ውለታ ከፍ ያለ ቦታ እንደነበረው ገልጸዋል፡፡ኢትዮጵያውያን በኮሪያዊያን ልብ ሁል ጊዜ ሲታወሱ ይኖራሉ ብለዋል፡፡ የኮሪያ መንግሥት ከኢትዮጵያን ጋር የ100 ሚሊዮን ዶላር የልማት ፕሮጀክት እያከናወነ መሆኑን አስታውሰው በጎንደር ከተማ በተለያዩ የልማት ሥራዎች ለመሳተፍ ዕቅድ እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታልን የጤና ግብዓት ለማሟላት የ200 ሺህ ዶላር ስምምነት መኖሩንም አስታውሰዋል፡፡
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ተወካይና በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የከተማ አስተዳደሩ የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ደብሬ የኃላ በበኩላቸው ሁለቱ ሀገራት 60 ዓመታትን ያስቆጠረ የታሪክ፣ የባሕልና የዲፕሎማሲ ግንኙነት እንዳላቸው አስታውሰዋል፡፡ የኮሪያ መንግሥት በከተማዋ በኢንቨስትመንት፣በቴክኖሎጅ ሽግግር፣በማኅበረሰብ አገልግሎትና በጤና ዘርፍ ድጋፍ ለማድረግ ፍላጎት በማሳደሩ ምሰጋና አቅርበዋል፡፡
በጎንደር ዪኒቨርሲቲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ኮሌጅ የማኅበረሰብ ጤና መምህርና ተመራማሪ ዶክተር አለማየሁ አጥናና ደግሞ ኮሪያውያን ከኢትዮጵያን ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከር በኢትዮጵያ ከሚገኙ ከተሞች ጋር በቅርበት እየሰሩ መሆኑን ገልጸው በአማራ ክልል በጦርነቱ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውን የጤና ተቋማት በማጠናከር ወደ ሥራ እንዲገቡ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ኮሪያ በጤና መድኅን ሥርዓት የተሻለ ተሞክሮ ያላት ሀገር በመኾኗ በቀጣይ ከኮሪያ መንግሥትጋር በቅንጅት እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡
አምባሳደሩ በጎንደር ከተማ ቆይታቸው በከተማዋ የሚገኙ ታሪካዊ ቦታዎችን እንደሚጎበኙ ከጉዟቸው መርኃ ግብር ለማወቅ ተችሏል ሲል የዘገበው የጎንደር ከተማ ኮሙኒኬሽን ነው ፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!