
አዲስ አበባ: ሰኔ 15/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ሁለተኛው ከፍተኛ “የአፍሪ ራን” ምክንያታዊ እና ፍትሀዊ የድንበር ተሻጋሪ ውኃ ሀብቶች አጠቃቀም ጉባዔ በአዲስ አበባ እየተካሔደ ነው። ጉባዔው ምክንያታዊ እና ፍትሐዊ የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች አጠቃቀም ለአፍሪካ ብልጽግና ወሳኝ ነው በሚል መሪ ሃሳብ ነው እየተካሔደ የሚገኘው።
በጉባዔው የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን “አፍሪ ራን” ባለፈው ዓመት ከተካሔደበት ከፍ ብሎ በሚኒስትሮች ደረጃም እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል። ይህ ጉባዔ ደንበር ተሻጋሪ ወንዞች የሚያጋጥማቸውን ተፈጥሮአዊ እና ሰው ሰራሽ ችግሮች መፍታት ዓላማ አንዳለው አስረድተዋል። ከእነዚህ መካከል ትልቁ ናይል አንዱ መኾኑን በመጥቀስ የጉባዔውን ሚና በማጠናከር ችግሮችን መፍታት ይገባል ብለዋል።
በወንዙ ለይ እየተገነባ የሚገኘው ታላቁ የህዳሴ ግድብም የፍትሐዊ እና ምክንያታዊ የውኃ አጠቃቀም ማሳያ መኾኑን አንስተዋል። ህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን በራሳችው አቅም እና ሃብት እየገነቡት ያለው ፕሮጀክት መኾኑን አንስተው። ይህ ደግሞ አፍሪካ ምን ያክል ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በራሳቸው አቅም መገንባት አንደሚችሉ ማሳያ ነው ብለዋል።
ጉባዔው ያለፈው ዓመት የቴክኒክ ኮሚቴ ባለሙያዎች እና የሚዲያ ሰዎች ብቻ ይሳተፉበት የነበረ ሲኾን በዚህ ዓመት ደግሞ የሚኒስትሮች ተሳትፎም ተጨምሮበታል። ተሳታፊ ሚኒስትሮቹ የፍትሀዊ እና ምክንያታዊ የውኃ አጠቃቀምን አንደሚደግፉ ገልጸው ለኢትዮጵያ ሳይኾን ለራሳቸውም ብለው የያዙት አቋም ስለመኾኑ ተገልጿል፡፡
የደቡብ ሱዳን የውጭ እና ዓለም አቀፍ ሚኒስትር ደንግ ሜልክ “ደቡብ ሱዳን ከምክንያታዊ የውኃ አጠቃቀም መርህ ጋር ትቆማለች” ብለዋል፡፡ የናይል ተፋሰስ ሀገራት የኢኮኖሚ አድገት በማምጣት እና ችግሮችን በመቅረፍ ናይልን ሊጠቀሙበት ይገባል ነው ያሉት። “የኢትዮጵያን ተጨባጭ ምክንያትም ሀገሬ ትደግፋለች” ነው ያሉት።
የኡጋንዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ምክትል ሚኒስትር ጆህን ሙላምቤ ዛሬ ምክንያታዊ እና ፍተሀዊ የውኃ አጠቃቀም ማጎልበት ስንል በአካባቢው ያለብንን የምግብ እጥረት እና ርሀብን ለመቅረፍ ያግዘናል ማለታችን እንደኾነ መገንዘብ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ የጀመረችው የአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም የውኃ አቅምን ለማጎልበት የሚረዳ በመኾኑ ሁላችንም ልንደግፈው ይገባል ነው ያሉት። የናይል ተፋሰስ ሀገራትም ምክንያታዊ እና ፍትሀዊ አጠቃቀምን መሰረት አድርገው ሃብቱን መጠበቅ እንደሚገባቸውም አስረድተዋል። ምክትል ሚኒስትሩ ጆህን ሙላምቤ “ሀገሬ ከፍትሀዊ የውኃ አጠቃቀም መርህ ጋር ትቆማለች” ብለዋል።
ዘጋቢ፡- አንዱዓለም መናን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!