የመደበኛ ቁርጥ ግብር ጥናት መደረጉ ግብር ከፋዩም ኾነ ግብር ሰብሳቢውን መሥሪያ ቤት የሚያግባባ አሠራር እንደሚኾን ተገለጸ፡፡

68

ባሕር ዳር: ሰኔ 15/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ 5ኛውን ዙር መደበኛ ቁርጥ ግብር ጥናት እያካሄደ ነው፡፡ ጥናቱ በሁሉም የአማራ ክልል ውስጥ በሚገኙ ወረዳዎች እና ከተማ አሥተዳደሮች የሚካሄድ ሲኾን የጸጥታ ችግር ባለባቸው ወረዳዎች ጥናቱ እንዳተጀመረ ተገልጿል፡፡

ታምራለች ውቤ በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳዳር የቀበሌ 11 ነዋሪ ናት። የባሕር ማዶ ኑሮን አይታዋለች ፡፡ የሄደችበት ባይሳካላትም ሀገሯ ገብታ ልቧ የፈቀደውን ለማድረግ ዛሬ ነገ አላለችም፡፡ ቋጥራ ያመጣችውን ጥሪት ወደ ውጤት ለመቀየር መሥራት የጀመረችው ከአንድ ዓመት ከስምንት ወር በፊት የሸቀጣ ሸቀጥ ሱቅ ከፍታ ሥራ ጀምራለች፡፡

ግብር መክፈል የዜግነት ግዴታ ነው ብላ የምታምነው ታምራለች ባለፈው ዓመት የስምንት ወር ግብር ከፍላለች፡፡ የከፈለችው ግብር ግን የተጋነነ ነው የሚል እምነት አላት፡፡ “በእየለቱ የምሸጠው ገንዘብ እና የምከፍለው ግብር አይመጣጠንም” የሚል ሀሳብም አላት፡፡ በመኾኑም አሁን እየተካሄደ ያለው የመደበኛ ቁርጥ ግብር ጥናት ከዚህ በፊት የነበሩ ችግሮችን ሊፈታ ይችላል የሚል እምነት እንዳላት ተናግራለች፡፡

ታምራለች ሰርቼ ከማገኘው ገቢ ግብር መክፈል አለብኝ ብላ ብታምንም በአካባቢዋ ካሉ ከሌሎች ነባር ነጋዴዎች ጋር ተመሳሳይ ክፍያ በመምጣቱ ቅሬታ ብታሰማም መልስ አለማግኘቷን ተናግራለች፡፡ ራስን ለማሥተዳደር እና ኑሮን ለማሸነፍ እየሠራሁ ነው የምትለው ታምራለች ቤተሠብን ማገዝ፣ ራስን ማሥተዳዳር ለራስ የተተወ በመኾኑ የሚጣልብን ግብር ራሳችንን የማይጎዳ እና የመንግሥትንም ገቢ የማይቀንስ የተመጣጠነ መኾን አለበት ብላለች፡፡

የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ምክትል ቢሮ ኀላፊ ክብረት ማህሙድ መደበኛ ቁርጥ ግብር ጥናት ከሦስት እስከ አምስት ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ የሚደረግ ጥናት ነው ብለዋል፡፡ አንድ ነጋዴ በመደበኛ ቁርጥ ግብር ጥናት ከተጠና ከሦስት እስከ አምስት ዓመት ተመሳሳይ ግብር ይከፍላል ማለት ነው፡፡ ይህም የደረጃ ሐ ግብር ከፋዮችን የሚመለከት ነው ብለዋል፡፡

አቶ ክብረት ጥናቱ ደረጃ ሐ እና አከራይ ተከራዮችን መሰረት ያደረገ ይሁን እንጂ ደረጃ ለ እና ሐ ይመለከታል ብለዋል፡፡ በዚህ ጥናት ከ460 ሺህ በላይ ተጠኝዎች ይሳተፉበታል፡፡

አቶ ክብርት ጥናቱ ካሁን በፊት ከተደረጉ ጥናቶች ለየት ለማድረግ ከገቢ ሰብሳቢው መሥሪያ ቤት ውጭ ያሉ አካላት የተካተቱበት አጥኝ ኮሚቴ ተዋቅሮ እየተካሄደ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ የሕዝብን የልማት እና የሰላም ጥያቄ ለመመለስ መንግሥት ከማንኛውም ሠርቶ ገቢ ከሚያገኝ አካል ገቢ ይሰበስባል ነው ያሉት፡፡

የንግዱ ማኅበረሰብ እውነታ ላይ የተመሰረተ መረጃ በመሥጠት መክፈል ያለበትን ግብር በአግባቡ መክፈል ይጠበቅበታል፤ ይህም ለሀገርም ለሕዝብም ጥቅሙ ብዙ ነው ብለዋል፡፡

ምክትል ቢሮ ኀላፊው በመረጃ ላይ ተመሥርቶ ግብር መጣሉ የማይቀር ጉዳይ በመኾኑ የንግዱ ማኀበረሰብ ቡድኑ በመጣበት ቀን ተገኝቶ መረጃ እንዲሠጥ ጠይቀዋል፡፡ ቁርጥ ግብር ጥናት አድራጊ ቡድኑ ተመላልሶ በመሄድ ድርጅቱ ላይ ያላገኘውን ግብር ከፋይ በአካባቢው ከሚገኙ ነጋዴዎች ጋር ተመሳሳይ ግብር የሚጣልበት አግባብ መኖሩንም ጠቁመዋል፡፡

መደበኛ ቁርጥ ግብር ጥናት ሲካሄድ ሽያጭን መሠረት የሚያደርግ ቢኾንም የአካባቢው መሠረት ልማት ምን ያህል የተሟላ ነው? ምን ያህል ደንበኛ አለው? ስሙ በደንበኞቹ ዘንድ ምን ያህል የታወቀ ነው? የሚለው ጉዳይ ታሳቢ እንደሚደረግ አቶ ክብረት አንስተዋል፡፡

ጥናቱ ግንቦት 24/2015 የተጀመረ ሲኾን ከ240 ሺህ በላይ ተጠኝዎች መረጃ መስጠታቸውን አንስተዋል፡፡ አቶ ክብርት ጥናቱን ዘግይተው የጀመሩ እና ያልጀመሩ ወረዳዎች መኖራቸውንም አንስተዋል፡፡ ጥናቱ ካሁን በፊት ይነሱ የነበሩ የቅሬታ ምንጮችን ሊቀንስ የሚችል እንደሚኾን መታሠቡንም ጠቁመዋል፡፡

መንግሥት ለማኀበረሰቡ የመሠረተ ልማት እና የሰላም ጥያቄ ለመመለስ የሚያስፈልገውን ገንዘብ የሚያገኝበት ከግብር ነው፡፡ የንግዱ ማኅበረሰብ ሠርቶ ካገኘው ገቢ ላይ የሚገባውን ግብር ለመንግሥት በመክፈል የልማቱ ተሳታፊ በመኾን ኀላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡

ማኅበረሰቡ ግብር ከፋዩ በእውነታ ላይ ተመሥርቶ ግብር እንዲከፍል የራሱን ድርሻ ሊወጣ ይገባል፡፡ ጥናቱ በግምት የሚሠራ በመኾኑም ትክክለኛው ግምት ባይሠራ እዚህ ላይ ስሕተት አለ በማለት መንግሥት ችግሩን እንዲያስተካክል ጥቆማ መሥጠት አለበት ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአሳሳቢው የትምህርት ቤቶቻችን ደረጃ ጉዳይ!
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ አረንጓዴ ልማት ሽግግር ለማድረግ ለሚያስፈልገው የገንዘብ ድጋፍ ጠንካራ ዘዴ መፍጠር እንደሚገባ ገለጹ።