አሳሳቢው የትምህርት ቤቶቻችን ደረጃ ጉዳይ!

67

ባሕር ዳር: ሰኔ 15/2015 ዓ.ም (አሚኮ) እውቁ የደቡብ አፍሪካ የነጻነት ታጋይ እና የቀደሞው የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ኔልሰን ማንዴላ “ዓለምን ለመለወጥ ከሚመረጡ ብልሃቶች መካከል ትምህርትን የሚያክል ብርቱ መሳሪያ አልተገኘም” ይላሉ፡፡ በሀገራት መካከል ለተፈጠረው ሳይንሳዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ እና ማኅበረሰባዊ መራራቅ እና መራቀቅ ትልቁ ምክንያት ለትምህርት የተሰጠ ልዩ ትኩረት እና ኢንቨስትመንት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ትምህርት ላቅ ያለ ልዩነትን በመፍጠር ረገድ እስካሁን ድረስ የሚወዳደረው አልተገኘም፡፡

ትምህርት ዑደታዊ እና ተፈጥሯዊ ሂደትን የሚከተል በመኾኑ ጠዋት ተዘርቶ ማታ የሚለቀም ፍሬ የለውም፡፡ “መማር የተምር ዛፍ እንደመትከል ይቆጠራል” ይላሉ ጥንታዊያኑ የምስራቁ ዓለም ሰዎች፡፡ ተምር የሚተክል አባት ውጤቱ ለልጁ እንጅ ለእርሱ እንደማይደርስ ያውቀዋል፡፡ ማስተማር ዓለምን መግለጥ ሲኾን መማር ደግሞ ዓለምን መመርመር እና ማወቅ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ዓለምን ለማወቅ የሚሞክሩ ተማሪዎች መነሻቸው ከትንሹ ተቋም ቤተሰብ እና ማኅበረሰብ እስከ ሰፊው የዓለም አጽናፍ ድረስ ይዘረጋል፡፡

የዘርፉ ምሁራን ለትምህርት የሰጡት ሳይንሳዊ ብያኔ እንደተጠበቀ ኾኖ መማር ማለት ዕውቀትን፣ ክህሎትን እና ግብረገብነትን አጣምሮ የያዘ እና ውጤቱም በተግባር የሚገለጽ ነው፡፡ የትምህርት ግቡ የሰውን ልጅ አስተሳሰብ መቅረጽ ሲኾን መለኪያው ደግሞ በተግባር የተገለጠ መሻሻል እና ዕድገት ነው፡፡ “ከመምህሩ ደቀመዝሙሩ” እንዲሉ ኢትዮጵያዊያን ልሂቃን ለውጥ እና ዕድገት የማይስተዋልበት ትምህርት መማር ሊባል አይችልም ይላሉ፡፡ ከትምህርት የሚጠበቀውን ለውጥ እና ዕድገት ለማምጣትም ትምህርት ላይ መጠነ ሰፊ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስን ይጠይቃል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት ገደማ የኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት ሳንካ ገጥሞታል ብለው የሚያምኑት በርካታ ናቸው፡፡ የትምህርት ሥርዓቱ ቁልፍ ችግሮች የመማር ማስተማር ባሕል ስብራት እና የትምህርት ጥራት ጉድለት ተደርገው ይወሰዳሉ፡፡ የትምህርት ጥራት አንጻራዊ ነው የሚሉት የትምህርት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት እና ጽሕፈት ቤት ኅላፊ አቶ ጌታቸው ቢያዝን የትምህርት ጥራት ችግር መኖሩ ግን አጠያያቂ አይደለም ነው ያሉት፡፡ የትምህርት ጥራት ችግር ዘርፈ ብዙ ምክንያቶች እንደነበሩበት በመጠቆም፡፡

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ያለፈውን አንድ ዓመት ሙሉ ወስዶ የትምህርት ሥርዓቱን ውስጣዊ እና ውጫዊ ችግሮች አጥንቷል፡፡ የትምህርት ሥርዓቱ ፈተናዎች እና የትምህርት ጥራት መሰናክል የኾኑ ችግሮች በበቂ ደረጃ በጥናት ላይ የተመሰረተ ልየታ ተደርጎባቸዋል የሚሉት የሕዝብ ግንኙነት ኅላፊው ለችግሮቹ መዋቅራዊ መልስ ለመስጠት የሚያስችል የ10 ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ተዘጋጅቷል ነው ያሉት፡፡ ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ እየተንከባለለ የመጣን የትምህርት ሥርዓት ችግር ጊዜ ወስዶ በማያዳግም መንገድ መፍታት ይገባል፡፡

አቶ ጌታቸው እንደሚሉት በቀጣይ ሦስት ዓመታት በልዩ ትኩረት የሚታዩ እና አፋጣኝ መልስ የሚሹ ጉዳዮች ተለይተው “የዜግነት አገልግሎት ለትምህርት ጥራት እና ተደራሽነት” የሚል ፕሮጀክት ተቀርጾ ወደ ትግበራ ለመግባት የክልሉን መንግሥት ይሁንታ ብቻ ይጠብቃል፡፡ የትምህርት ጥራት ችግሮችን በቁርጠኝነት ለመፍታት ካስፈለገ ፕሮጀክቱን በርብርብ መሬት ማውረድ ይጠይቃል የሚሉት የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያው የፌዴራል እና የክልሉ መንግሥት፣ የትምህርት ባለድርሻ አካላት፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እና ወላጆች ለተፈጻሚነቱ የየድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል ነው የሚሉት፡፡

ትምህርት በሰጡት እጥፍ የሚመልስ፣ ረጅም ጊዜን የሚጠይቅ እና ክትትልን የሚሻ ዘርፍ ነው ያሉት አቶ ጌታቸው በአማራ ክልል ለትምህርት ጥራት መጓደል ምክንያት ከኾኑት መካከል የግብዓት እጥረት ተጠቃሽ ነው ይላሉ፡፡ የትምህርት ቤት ደረጃ መሻሻል እና ለተማሪዎች መማር ምቹ አካባቢን መፍጠር ትልቅ ልዩነት የሚፈጥር ለውጥ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ከዚህ አንጻር ሲታይ በክልሉ የትምህርት ቤቶች ደረጃ አሳሳቢ እንደኾኑ እና ከ80 በመቶ በላይ የሚኾኑት ትምህርት ቤቶች ከደረጃ በታች ስለመኾናቸው ይገልጻሉ፡፡

የትምህርት ቤቶች ደረጃ “ከደረጃ በታች ነው” እያሉ መዝለቅ ትርጉም እንደሌለውም አቶ ጌታቸው ተናግረዋል፡፡ የሦስት ዓመት ፕሮጀክት የኾነው የዜግነት አገልግሎት ለትምህርት ጥራት እና ተደራሽነት ችግሩን ለመፍታት አልሞ የተዘጋጀ ነው ብለዋል፡፡ ጥናቱ እንደሚያመላክተው 84 በመቶ የቅድመ መደበኛ፣ 87 በመቶ የመጀመሪያ ደረጃ እና 82 በመቶ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከደረጃ በታች ናቸው፡፡

የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል በቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት የትምህርት ቤቶች ግንታ ልዩ ትኩረት ያስፈልገዋል ያሉት የሕዝብ ግንኙነት ኅላፊው ትልቅ ዕቅድ፣ መጠነ ሰፊ የማኅበረሰብ ተሳትፎ፣ ሰፊ ሃብት እና ረጅም ጊዜ ወስዶ መፈጸም ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡ ዕቅዱ እንዲሳካም የሁሉንም አካላት ድርሻ እና ትብብር ይጠይቃል ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleደብረ ብርሃን የሚገኘው የበላይነህ ክንዴ ግሩፕ የመኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካ ከ250 በላይ ለሚደርሱ ወገኖች የሥራ እድል መፍጠሩን ገለጸ።
Next articleየመደበኛ ቁርጥ ግብር ጥናት መደረጉ ግብር ከፋዩም ኾነ ግብር ሰብሳቢውን መሥሪያ ቤት የሚያግባባ አሠራር እንደሚኾን ተገለጸ፡፡