
ባሕር ዳር: ሰኔ 15/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ሽምግልና የኢትዮጵያውያን ዘመን ተሻጋሪ ትልቁ ባሕላዊ እሴት ነው። ሽምግልና የሚፈጠሩ ግጭቶችንና አለመግባባቶችን በአስታራቂ ሽማግሌዎች በእርቅ በመፍታት፤ የተበደለን ክሶ የበደለን ደግሞ ወቅሶ ሁለቱንም ወገን አሸናፊ የሚያደርግ ተመራጩ ባሕላዊ ሥርዓት ስለመኾኑም ነው የሚነገረው። እናም ድንገት ከሚፈጠሩ ግጭቶችና አለመግባባቶች እስከ ኾን ተብሎና ታቅዶ የሚፈጸም የወንጀል ድርጊትን በባሕላዊ የሽምግልና ሥርዓት በእርቅ መፍታት የተለመደ ተግባር ነው።
ግጭትና አለመግባባትን በሽምግልና መፍታት በፍርድ ቤቶች የሚፈጠርን መጨናነቅና የሥራ መብዛት በመቅረፍ በኩል ጉልህ ድርሻ እያበረከተ መኾኑን የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ገልጿል። አለመግባባቶችን በሽምግልና በእርቅ እልባት የመስጠት ተግባር ከተከራካሪ ወገኖች እስከ ፍርድ ቤቶች ፋይዳው የጎላ ነው የሚሉት የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ታዘባቸው ጣሴ ናቸው።
የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊው ለአሚኮ እንደተናገሩት ባለፉት 11 ወራት በአማራ ክልል ወደ ፍርድ ቤት ከመጡ መዝገቦች መካከል 29 ሺህ 213 ጉዳዮች በሽምግልና በእርቅ ተፈትተዋል ብለዋል። በክልሉ በየደረጃው ባሉ ፍርድ ቤቶች በዓመት ከ700 ሺህ በላይ ጉዳዮች በፍርድ ቤት ይታያሉ የሚሉት አቶ ታዘባቸው የክስ መዝገቦችን ተመልክቶ እንደየጉዳዩ በሽምግልና እንዲታዩ ለተከራካሪ ወገኖች አቅጣጫዎችን መስጠት የፍርድ ቤቶች ቀዳሚ ተግባር እንደኾነም አስረድተዋል።
የባለጉዳዮችን ችግር በእርቅ መፍታት ጠቀሜታው ለባለጉዳዩም፣ ለፍርድ ቤቱም ነው የሚሉት ኀላፊው ባለጉዳዮች የፍርድ ሂደት በሚኖር ጊዜ በቀጠሮ መንገላታትን ፣ ያልተገባ ወጭን ያስቀራል ፣ለፍርድ ቤቶችም በሐሰተኛ ሰነድና በሐሰት ምስክር ሊፈጠር የሚችልን የፍትሕ መዛባት በማስወገድ ረገድም ትልቅ ድርሻ አለው ነው ያሉት። በጉዳዩ ላይ የሚቀመጡ ሽማግሌዎች የሁለቱንም ተከራካሪ ወገኖች ጉዳይ በቅርበት የሚያውቅ በመኾኑ ፍትሕ እንዳይዛባ ያደርጋል ብለዋል።
ከዚህም ባሻገር በፍርድ ቤት የዳኝነት ሂደት ውስጥ የሚኖርን የጊዜ ቀጠሮና እንግልት፣ ወጭንም ጭምር ይቀንሳል በመኾኑም ጉዳይን በሽምግልና ማየት ይገባል ነው የሚሉት አቶ ታዘባቸው።
በሌላ በኩል ሁለቱም አካላት አሸናፊ የሚኾኑበት የፍርድ ሂደት ተግባራዊ የሚደረገው በሽምግልና ሥርዓት ነው።
“አንተም ተው አንተም ተው “ብሎ ማስታረቅ በገጠመው አለመግባባትና ግጭት የሚፈጠርን በቀል፣በእልሕና አልረታም ባይነት የሚከተልን ጥፋት ይቀንሳል።
የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊው አቶ ታዘባቸው እንደሚሉት ወደ ፍርድ ቤት ከሚመጡ ጉዳዮች ፍርድ ቤቱ በእርቅ እንዲፈቱ ሃሳብ ሲያቀርብ ጉዳዩን በእርቅ ለመፍታት ሁለቱን ተከራካሪ ወገኖች በቀናነት እንደሚያዩት ነው የተናገሩት።
ግጭትንና አለመግባባትን በባሕላዊ የሽምግልና ሥርዓት መፍታት ማኅበራዊ ትስስርን በማንበር ፣አንድነትን በማምጣት፣ የሐሰት ምስክርንና የሐሰት ሰነድ ማቅረብን ለመከላከል ሚናው የጎላ ነውና ኹሉም ጉዳዩን በሽምግልናና በእርቅ መፍታትን በመምረጥ ኀላፊነቱን እንዲወጣ አሳስበዋል።
ዘጋቢ :- ጋሻው አደመ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!