
ደብረ ታቦር: ሰኔ 15/2015 ዓ.ም (አሚኮ) እያንዳንዳቸው 300 ሺህ ብር ዋጋ ያላቸው ሁለት ጀልባዎች ናቸው ለደቡብ ጎንደር ዞን የደራና ፎገራ ወረዳ ጎርፍ ለሚያጠቃቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ነው ድጋፍ የተደረገው፡፡ ኮሊሽን ቻይልድ ሳፖርት አሶሴሽን የተባለ ሀገር በቀል በጎ አድራጊ ድርጅት ያደረገውን ድጋፍ የዞን እና የወረዳ አመራሮች በደራ ወረዳ ጉማራ ወንዝ ላይ በመገኘት ተረክበዋል፡፡
በደቡብ ጎንደር ዞን ምዕራባዊ ወረዳዎች በክረምት ወራት፣ የርብና ጉማራ ወንዞች ከገደባቸው ሞልተው በመፍሰስና በአካባቢው ባለው ከፍተኛ የውኃ መጠን ምክንያቶች አካባቢው በጎርፍ መጥለቅለቁ የተለመደ ክስተት ነው፡፡ አደጋው ነዋሪዎቹን ከቀያቸው የሚያፈናቅል ሲኾን ለውኃ ወለድ በሽታም ያጋልጣል፡፡
በመኾኑም ኮሊሽን ቻይልድ ሳፖርት አሶሴሽን የተባለ ሀገር በቀል በጎ አድራጊ ድርጅት ችግሩ ሲከሰት ነዋሪዎቹን ከአደጋው ለማሸሽና ሌሎች ድጋፎችን ለማድረግ የሚያስችሉ ሁለት ጀልባዎችን ለደራና ፎገራ ወረዳዎች ድጋፍ አድርጓል፡፡
አስተያየታቸውን ለአሚኮ የሰጡ የወረዳዎቹ ነዋሪዎች አደጋው ሲከሰት ሕፃናትና አረጋዉያን የበለጠ ለችግር እንደሚጋለጡ ገልጸው ጀልባዎቹ በመኖራቸው የሰው ሕይዎትም ኾነ ንብረት ሳይጎዳ ለማውጣት እንደሚጠቅም ገልጸዋል፡፡
በደራ ወረዳ ሦስት ቀበሌዎች በጉማራ ወንዝ የመጥለቅለቅ አደጋ አለባቸው ያሉት በወረዳው ግብርና ጽሕፈት ቤት የቅድሚያ ማስጠንቀቂያና ፈጣን ምላሽ ቡድን መሪ አበበ ተድላ አደጋው ሲያጋጥም ኅብረተሰቡን ከቦታው ለማውጣት ጀልባው ወሳኝ መኾኑን ተናግረዋል፡፡
ድጋፉን ያደረገው የኮሊሽን ቻይልድ ሳፖርት አሶሴሽን በጎ አድራጊ ድርጅት መሥራችና ሥራ አሥኪያጅ አዲሱ ይልሃል ድርጅታቸው በአርሊ ዋርኒንግ ሪስፖንስ ፕሮጀክት አማካይነት ጀልባዎቹን መደገፉን ተናግረዋል፡፡ የበጀቱ ድጋፍ የተገኘውም ወርልድ ጂዊሽ ሪሊፍ ከተሰኘ በጎ አድራጊ መኾኑን ጠቁመዋል፡፡
የዞኑ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ በላይ አስራደ ከጽሕፈት ቤታቸው ሥራዎች መካከል አደጋን ቀድሞ መከላከል አንዱ መኾኑን ጠቅሰው ድጋፉ በጎርፍ የመጥለቅለቅ አደጋ ያለባቸውን ወረዳዎች ኅብረተሰብ ለማገዝ ያለመ ነው ብለዋል፡፡
የብልጽግና ፓርቲ የደቡብ ጎንደር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ጥላሁን ደጀኔ በዞኑ ከአደጋ መከላከል ሥራዎች አኳያ የጎርፍ ተጠቂዎችን ለመደገፍ የሚሠራው ሥራ አንዱ መኾኑን ገልጸው ለጋሽ ድርጅቱ ለዚሁ ሥራ ላደረገው ድጋፍ አመሥግነዋል፡፡
ጀልባዎቹ የጎርፍ ተጠቂዎችን ከአደጋው ከማውጣት በተጨማሪ የሕክምናና ሌሎች ድጋፎችን ለማድረስ፣ የበሽታ ቅኝትና ቁጥጥር ለማድረግ እንደሚያገለግሉም በርክክብ ሥነ ሥርዓቱ ተገልጿል፡፡
ዘጋቢ፦ ዋሴ ባየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!