
ባሕር ዳር: ሰኔ 15/2015 ዓ.ም (አሚኮ) አምስት የውጭ ሀገር ባንኮች ኢትዮጵያ ውስጥ ገብተው አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችላቸው ፈቃድ እንደሚሰጣቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ።
ሀገር በቀል ባንኮች ከወዲሁ ከፍተኛ ዝግጅት ማድረግ እና ቀድሞ የነበራቸውን ስትራቴጂ መከለስ እንዳለባቸውም አሳስቧል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ተቋማት ዘርፍ ምክትል ገዥ አቶ ሠለሞን ደስታ ከኢፕድ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ የሀገር ውስጥ የፋይናንስ ተቋማትን ከማጠናከር ጎን ለጎንም የውጭ ባንኮችን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት እየተሠራ ነው።
‹‹ሥራውን አሁን እያጠናቀቅን ነው። አዋጁን የመከለስ ሥራውንም እያጠናቀቅን ነው:: ከለጋሾች አንዳንድ ግብዓቶችን እየጠየቅን ነው። በወራት ዕድሜ ለሕዝብ እንደራሴዎች ይቀርባል:: ስለዚህ ሥራው እየተፋጠነ ነው” ብለዋል አቶ ሠለሞን።
በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ከሦስት እስከ አምስት ለሚደርሱ የውጭ ባንኮች ፈቃድ ለመስጠት እቅድ ተይዞ እየተሠራ መሆኑንም አቶ ሠለሞን ገልጸዋል።
እንደ ምክትል ገዥው ገለጻ፤ የውጭ ባንኮች የሀገር ውስጥ ባንኮችን ከገበያ እንዳያስወጧቸው የሀገር ውስጥ የፋይናንስ ተቋማት አቅም ግንባታ ላይ ሊሠሩ ይገባል፤ለዚህም የተቀመጠ አሠራር መኖሩን አመልክተዋል።
ተቋማቱ ከመደበኛ በጀታቸው ሁለት ከመቶ የሚሆነውን ለአቅም ግንባታ እንዲያውሉትና ይህም ለባንኮች ከረጅም ዓመታት በፊት የተላለፈ መሆኑን፣ አሁንም ድረስ በዚሁ አግባብ ክትትል እንደሚደረግ አቶ ሠለሞን አስረድተዋል።
አሁን ቀድሞ እንደተለመደው መሄድ አይቻልም ያሉት አቶ ሠለሞን፣ ሪፎርም ከተደረገ ወዲህ ብዙ አዳዲስ ነገሮች አሉ፤ በጀት ተመድቦም በሰፊው መሥራት አስፈላጊ ነው ብለዋል።
“በተለይም ማን ከማን ጋር መሥራት አለበት፤ ማን ከማን ጋር ቢዋሃድ ያዋጣል የሚለውን ከአሁኑ ማሰብ ይገባል:: ከውጭ ከሚመጡ ተቋማትም ጋር እንዴት በቅንጅት መሥራት እንዳለባቸው ከወዲሁ ማሰብ ይጠበቅባቸዋል፤ ካፒታል፣ ዕውቀት እና ቴክኖሎጂ እንዴት መጋራት እንደሚቻልም ባንኮቹ ከወዲሁ ሊያጤኑት ይገባል:: በተጨማሪም ሌሎች ባንኮችን ሄደው መጎብኘት አለባቸው” ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
በተለይም የቦርዱ አመራርና አሠራር፣ ማኔጅመንቱ የሚያስተዳድርበትን መንገድና ሥርዓት፣ የሕግ ማዕቀፎች፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምና የሰው ኃይል አስተዳደር ጭምር ማወቅ ተገቢ መሆኑን አሳስበዋል።
ወደዚህ ሥራ ለመግባትም የፋይናንስ ተቋማት ካፒታላቸውን ማሳደግ እንዳለባቸው የገለጹት ምክትል ገዥው፤ ቀደም ሲል የነደፉትን ስትራቴጂ ብቻ መጠቀም ሳይሆን መልሰው ማየትና መከለስ አለባቸው፤ ከሚመጣው ሁኔታ አኳያ እነዚህንና ሌሎች ሁኔታዎችን ታሳቢ የሚያደርጉ ጉዳዮችን በሙሉ ጥንቃቄ በተሞላው መንገድ መሥራት ይገባል ሲሉም ጠቅሰዋል።
እንደ ኢፕድ ዘገባ በአጠቃላይ ባንኮች መጪውን ጊዜ እና ቴክኖሎጂ ማዕከል ያደረገ ሥራ እና አቅም መገንባት ብሎም በዘርፉ ላይ የተሻለ ልምድና ዕውቀት አካብተው መገኘት እንዳለባቸው አቶ ሠለሞን አሳስበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!