“ሕዝቡ የሚያነሳቸውን ቅሬታዎች መፍታት የሁሉም ተቋማት ዋነኛ ተግባር ሊሆን ይገባል” የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ጽሕፈት ቤት

31

እንጅባራ: ሰኔ 14/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ሕዝቡ የሚያነሳቸው የአግልግሎት አሰጣት ችግሮች ላይ የሚነሱ ቅሬታዎች በወቅቱ እና ተገቢ ምላሽ እያገኙ አለመሆኑን በዘርፉ የተደረጉ ጥናቶች ያመለክታሉ።

የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ጽሕፈት ቤት ከክልሉ የሕዝብ ቅሬታ ሰሚ ጽሕፈት ቤት ጋር በመቀናጀት ሕዝቡ የሚያነሳቸውን ቅሬታዎችን እንዲሁም የቅሬታ ምንጮችን ለይቶ ውሳኔና ተገቢ ምላሽ በመስጠት በኩል አየተሠራ ያለውን ሥራ አስመልክቶ የጥናት ቡድን አሰማርቶ የቅሬታ ምንጮችን ፍተሻ አድርጓል።

የፍተሻ ሥራውን ከ4 የክልል ቢሮዎች ጀምሮ እስከ ታች ድረስ አድርጓል። ይህንን ጉዳይ የቢሮ ኀላፊዎች ፣የዞን አመራሮች፣ ጉዳዩ የሚመለከታቸው በተገኙበት የግኝት ውጤቶች ዙሪያ ውይይት እና እንዴት ይፈታሉ ለቀጣይስ ምን አቀጣጫ ይቀመጥ በሚል የውይይት መድረክ በእንጅባራ ከተማ አካሂዷል።

የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ወይዘሮ ሳላማዊት ዓለማየሁ እንዳሉት የክልሉ ሕዝብ በአግልግሎት አሰጣት ላይ በርካታ ቅሬታዎችን በማንሳት ላይ ይገኛል ነው ያሉት።

ሕዝቡ የሚያነሳቸውን ቅሬታዎች መፍታት የሁሉም ተቋማት ዋነኛ ተግባር ሊሆን እንደሚገባ የገለፁት ኀላፊዋ፤ መፍትሄ ያጣ ሕዝብ ወደ ቀውስ መግባቱ አጠያያቂ አይሆንም ብለዋል።

በተለይ የሕዝብን ስልጣንና ኀላፊነት የያዘ አመራር የሕዝቡ የቅሬታ ምንጮችን ለይቶ መፍትሄ እና ውሳኔ በመስጠት ተገቢውን አግልግሎት መስጠት ወቅቱ የሚጠይቀው ገዳይ መሆኑን ጠቁመዋል።

የጥናት ቡድኑ በክልሉ 4 ቢሮዎች ማለትም ንግድ ቢሮ፣ ሥራና ስልጠና፣ ከተማ ልማት እና መሬት አሥተዳደር ቢሮዎች በተዋረድ እስከ ቀበሌ ጥናት መደረጉን የገለፁት ደግሞ የክልሉ የሕዝብ ቅሬታ ሰሚ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አቶ ሙሉጌታ ደባሱ ናቸው።

በተደረገው ጥናት የተገኙ ግኝቶች የሚያሳዩት ሕዝቡ በአግልግሎት አሰጣት ችግር መማረሩን፣ተገቢ ምላሽ እንደማያገኝ፣ መመላለሶች እንዳሉ፣ አለመደመጥ ችግር፣ አመራሩ ቢሮ ተገኝቶ ምላሽ አለመስጠት በስፋት ተስተውለዋል ነው ያሉት አቶ ሙሉጌታ።

ሕዝቡ ቅሬታ የሚያነሳባቸው ተቋማት ለምን ቅሬታ ምንጭ ሆንን በሚል ችግሮችን ለመፍታት አሠራሮችን በመቀየስ ከሕዝብ ቅሬታ ሰሚ ተቋማት ጋር ተቀናጅተው መሥራት የሁሉም ተቋማት ኀላፊነት መሆን አለበት ብለዋል የጽሕፈት ቤት ኀላፊው።

በ 8 ዞኖች እና በ135 ወረዳዎች ጥናት መደረጉን የገለፁት አቶ ሙሉጌታ፤ ሕዝቡ በሚያነሳው ቅሬታ ልክ ጊዜና ጉልበት ሳያባክኑ በያሉበት ተገቢውን አግልግሎት እና ለችግሮቹ የመፍትሄ አቅጣጫ እያስቀመጡ ሁሉንም አካል ማገልገል ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።

ዘጋቢ፦ሰለሞን ስንታየሁ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የሀገር አቀፍ እና ክልል አቀፍ ማጠቃለያ ፈተናዎችን ለመስጠት የሚያስችል በቂ ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል” የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ
Next articleበ12 ክለቦች መካከል ሲካሄድ የቆየው የአማራ ሊግ ቮሊቦል ውድድር በባንጃ ክለብ አሸናፊነት ተጠናቀቀ።