“የሀገር አቀፍ እና ክልል አቀፍ ማጠቃለያ ፈተናዎችን ለመስጠት የሚያስችል በቂ ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል” የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ

77

ባሕር ዳር: ሰኔ 14/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ከሰኔ 26/2015 ዓ.ም እስከ ሐምሌ 30/2015 ዓ.ም ድረስ የሀገር አቀፍ እና ክልል አቀፍ ማጠቃለያ ፈተናዎች ይሰጣሉ፡፡ በክልል ደረጃ የሚሰጠውን የ8ኛ ክፍል እና በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚሰጠውን የ12ኛ ክፍል ማጠቃለያ ፈተና ለመስጠት የሚያስችል በቂ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታውቋል፡፡

በ2015 ዓ.ም የትምህር ዘመን በአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ሥር 5 ሺህ 752 አስፈታኝ ትምህርት ቤቶች ለ8ኛ ክፍል ማጠቃለያ ፈተና መዘጋጀታቸውን የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት እና ጽሕፈት ቤት ኅላፊ አቶ ጌታቸው ቢያዝን ገልጸዋል፡፡ ለ8ኛ ክፍል አስፈታኞች በክልል ደረጃ የግንዛቤ ማስጨበጫ ገለጻ መሰጠቱን የገለጹት አቶ ጌታቸው በቀሪ ጊዜያት እስከ ትምህርት ቤት ድረስ ኦረንቴሽን ይሰጣል ብለዋል፡፡

የተማሪዎች ምዘና በአዲሱ የትምህርት ሥርዓት መሠረት የሚፈጸም ነው ያሉት የሕዝብ ግንኙነት ኅላፊው ተማሪዎችን ለፈተና ብቁ ለማድረግ የሚደረጉ እገዛዎች አበረታች ናቸው ብለዋል፡፡ በክልሉ 347 ሺህ 966 ተማሪዎች የ8ኛ ክፍል ማጠቃለያ ፈተናውን ይወስዳሉ ተብሏል፡፡

እንደ አቶ ጌታቸው ገለጻ ከሐምሌ 19 /2015 ዓ.ም እስከ ሐምሌ 30 / 2015 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ይሰጣል፡፡ የ12ኛ ክፍል ማጠቃለያ ፈተናው የሚሰጠው እንዳለፈው ዓመት ሁሉ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት (ዩኒቨርሲቲዎች) ውስጥ ነው ተብሏል፡፡ ፈተናው ከተቀመጠለት ግብ አንጻር በስኬት እንዲጠናቀቅ የትምህርት ባለ ድርሻ አካላት በትኩረት እየሰሩ መኾናቸውንም አቶ ጌታቸው ነግረውናል፡፡

በክልሉ 215 ሺህ 570 የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ሀገር አቀፍ የማጠቃለያ ፈተናውን ይወስዳሉ ተብሏል፡፡ ካለፈው ዓመት የ12ኛ ክፍል ፈተና ትምህርት በመውሰድ ተማሪዎች የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ፤ በተለይም ደግሞ በሥነ-ምግባራቸው ምስጉን እና አርዓያ እንዲኾኑ ተሠርቷል ያሉት አቶ ጌታቸው በየደረጃው ከሚገኙ የትምህርት ባለድርሻ አካላት እና ከተማሪዎች ጋር ተደጋጋሚ ውይይቶች ተደርገዋል ነው ያሉት፡፡

ተፈታኝ ተማሪዎችን በሥነ-ልቦና በማዘጋጀት በኩል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እየሠሩት ያለው ሥራ አበረታች ነው፡፡ ፈተናው የሚሰጠው በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በመኾኑም በቂ ዝግጅት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleነፋስመውጫ ከተማ አሥተዳደር በ56 ሚሊዮን ብር የተገነቡ ፕሮጀክቶች ተጠናቅቀው ለአገልግሎት ክፍት ኾኑ፡፡
Next article“ሕዝቡ የሚያነሳቸውን ቅሬታዎች መፍታት የሁሉም ተቋማት ዋነኛ ተግባር ሊሆን ይገባል” የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ጽሕፈት ቤት