
ደብረ ታቦር: ሰኔ 14/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በዓለም ባንክ የመሠረተ ልማት እና በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ማልማት ፕሮጀክቶች የተሠሩ የነፋስመውጫ ከተማ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ተጠናቅቀው ተመርቀዋል፡፡
በደቡብ ጎንደር ዞን ነፋስመውጫ ከተማ በዓለም ባንክና በመንግሥት የመቀናጆ በጀት የተሠሩ መሠረተ ልማት ሥራዎችና በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ በማልማት ፕሮግራም የተገነቡ የልማት ሥራዎች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ኾነዋል፡፡
መሠረተ ልማቶቹ ከመሠራታቸው በፊት ይቸገሩ እንደነበር የተናገሩት የነፋስመውጫ ከተማ ነዋሪዎች አሁን ላይ መንገዶቹ በመገንባታቸው ችግራቸው እንደተቀረፈ ተናግረዋል፡፡
የነፋስመውጫ ከተማ ከንቲባ ሙላው ጤናው ከጦርነት ማግስት ከተማዋን መልሶ ለማልማት በቁጭትና በእልህ በመሠራቱ የተሻለ ውጤት መገኘቱን ገልጸዋል፡፡
12 ፕሮጀክቶች በአዲስ፣ 12 ፕሮጀክቶች ደግሞ በጥገና መሠራታቸውን የተናገሩት ከንቲባ ሙላው ከእነዚህም ውስጥ የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ፣ የጠጠር መንገድ፣ የውኃ ማፋሰሻ ቦይ፣ የውኃ መስመር ዝርጋታ፣ መጸዳጃ ቤትና፣ ክላስተር ሸድ እንደሚገኙበት ነው ያስገነዘቡት፡፡
በአማራ ክልል በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎች መልሶ ማቋቋምና ግንባታ ፈንድ ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አሥኪያጅ አባተ ጌታሁን (ዶ.ር) በክልሉ በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለማልማት 105 የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ መኾኑን ጠቅሰው ከዚህ መካከልም ሁለቱ በነፋስመውጫ ከተማ ተገንብተው የተጠናቀቁት የጤናና የትምህርት ግንባታዎች መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡ ዶክተር አባተ አክለውም ሕዝብና መሪ ተቀናጅቶ በመሥራቱ ፕሮጀክቶቹ በፍጥነት መጠናቀቃቸውን ጠቅሰዋል፡፡
የአማራ ክልል ከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ ምክትል ኀላፊ ሱሌማን እሸቱ በበኩላቸው ነፋስመውጫ ከተማ በጦርነት በመጎዳቱ መልሶ ለማልማት የተሠራው ሥራ አበረታች መኾኑን ተናግረዋል፡፡ ምክትል ቢሮ ኀላፊው በክልሉ ከተሞችን ለማልማት በበጀት ዓመቱ የዓለም ባንክን ፕሮጀክት ሳይጨምር 848 ፕሮጀክቶች በሕዝብ ተሳትፎ በ900 ሚሊዮን ብር እየተሠሩ መኾናቸውን አብራርተዋል፡፡ የዘንድሮን ጨምሮ ባለፉት 5 ዓመታት 4 ሺህ 189 ፕሮጀክቶች በ10 ቢሊዮን ብር ተገንብተው መጠናቀቃቸውንም ነው የገለጹት፡፡
የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ይርጋ ሲሳይ ዞኑ በርካታ የተፈጥሮ ሃብቶች ያሉት መኾኑን ጠቅሰው ይህንን ሃብት ይዞ ለመልማት ሁልጊዜ በእርዳታ ላይ ጥገኛ መኾን አይገባውም ብለዋል፡፡
አቶ ይርጋ የተጀመሩ የልማት ሥራዎች እንዲስፉ ኅብረተሰቡን ማንቀሳቀስና ምቹ የሥራ ሁኔታ መፍጠርም እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ አመራሩና ሕዝቡ ተናቦ የተፈጥሮ ሃብትን በማልማት ከእርዳታና ብድር ጥገኝነት መላቀቅ እንደሚገባም ነው ዋና አሥተዳዳሪው ያስገነዘቡት፡፡
ዘጋቢ፦ ዋሴ ባየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!