
ባሕር ዳር: ሰኔ 14/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የደቡብ ጎንደር ዞን አርሶ አደሮች 10 ዘመናዊ የእርሻ ትራክተሮችን በመግዛት ወደ ዞኑ አስገብተዋል። አርሶ አደሮቹ ትራክተሮችን ከአማራ ብረታ ብረትና ማሽን ቴክኖሎጂ ልማት ድርጅት ተረክበዋል። በርክክቡ ላይ የተገኙት የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ይርጋ ሲሳይ ዞኑ ሁሉንም አይነት ሰብሎችን የሚያመርት እና ለትራክተር እርሻ ምቹ የኾነ ዞን ነው ብለዋል። በተለይም ፎገራ፣ አንዳቤት፣ እስቴ፣ ስማዳ፣ ጋይንት እና ሌሎችም ወረዳዎች ለዘመናዊ የትራክተር እርሻ ምቹ ናቸው ብለዋል።
ዋና አሥተዳዳሪው በዞኑ ከዚህ በፊት 10 ትራክተሮች ብቻ እንደነበሩ ገልጸዋል። ዛሬ ደግሞ 10 ተጨማሪ ትራክተሮች በአርሶ አደሮች ተገዝተው ወደ ዞኑ ገብተዋል ብለዋል። አቶ ይርጋ “በምግብ ሰብል ራስን ችሎ ከድኅነትም ለመውጣት ግብርናችንን ማዘመን ግድ ይላል” ሲሉ ተናግረዋል። ዛሬ በአርሶ አደሮች የተገዙ ትራክተሮችም በዞኑ የተጀመረውን ዘመናዊ የእርሻ እንቅስቃሴ ለመደገፍ ያግዛሉ ብለዋል። በርከት ያሉ ትራክተሮች ወደ ዞኑ መግባታቸው አርሶ አደሮች ሰብሎችን በኩታ ገጠም እንዲያመርቱ ተጨማሪ እድል የሚፈጥር ስለመኾኑም ገልጸዋል።
“በግብርናው ዘርፍ ውጤት ለማስመዝገብ ትራክተር መግዛት ብቻ በቂ አይደለም” ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው በየደረጃው ያሉ የግብርና ባለሙያዎች ክትትል በማድረግ አርሶ አደሮችን መደገፍ አለባቸው ብለዋል። አርሶ አደሩም የላቀ የአመለካከት ለውጥ በማምጣት መሬቱን በዘመናዊ መንገድ አርሶ ትርፍ የማምረት ልምድ ማካበት አለበት ሲሉ ዋና አሥተዳዳሪው መልእክት አስተላልፈዋል።
ተጨማሪ ትራክተር መግዛት ለሚፈልጉ አርሶ አደሮች የብድር አቅርቦት እንደሚመቻችም ተናግረዋል።
ትራክተሮችን ከገዙ አርሶ አደሮች መካከል ወይዘሮ የውብዳር ስንታየሁ ሀገር እንድታድግ ከተፈለገ ዘመናዊ የአስተራረስ ዘዴን መከተል ያስፈልጋል ብለዋል። በፎገራ ወረዳ በአትክልት እና ፍራፍሬ የመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸውም ገልጸዋል። ወይዘሮ የውብዳር ከዚህ በፊት ሁለት ትራክተሮች እንደነበሯቸው ገልጸው በዛሬው ዕለት ደግሞ ሌላ ሁለት ተጨማሪ ትራክተሮችን ገዝተዋል። ትራክተሮች ዘመናዊ እርሻን በማሳለጥ ለውጤታማነት እንደሚያበቋቸውም ገልጸዋል። በቀጣይም የሰብል ማጨጃና መውቂያ ኮንባይነር በመግዛት ሙሉ በሙሉ ወደ ዘመናዊ እርሻ እንደሚገቡ ተናግረዋል።
ሌላው አርሶ አደር ጌታቸው ወርቁ ዛሬ የገዙት የትራክተር ዋጋ 80 በመቶው በልማት ባንክ አበዳሪነት የቀረበ ሲኾን 20 በመቶው ደግሞ በራሳቸው ወጪ ስለመኾኑ ነው የገለጹት። ትራክተሩ በበሬ አንገት ከሚከናወነው የአስተራረስ ዘዴ ለመላቀቅ እና የተሻለ ምርት ለማግኘት እንደሚያስችልም አርሶ አደሩ ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!