
ባሕር ዳር: ሰኔ 14/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ለእናቶች ሞት ዋነኛው ምክንያት የደም መፍሰስ መኾኑን የኢትዮጵያ ደምና ሕብረ-ህዋስ ባንክ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሀብታሙ ታዬ ገልጸዋል።
የደም መፍሰስ ችግርን ጨምሮ አሁን ላይ ያለደም ሕክምና ለማድረግ የማይታሰቡ እንደ ካንሰር የመሳሰሉ ተላላፊ ያልኾኑ በሽታዎችን ለማከም ከክልል ደም ባንኮች ጋር በመተባበር ከበጎ ፈቃድ ደም ለጋሾች ደም በማሰባሰብ ለሕክምና ተቋማት እየተሰራጨ መኾኑን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
አቶ ሀብታሙ እንዳሉት በአንድ ሀገር የደም ፍላጎት የተሟላ ነው የሚባለው ቢያንስ ከሀገሪቱ ሕዝብ አንድ ወይም ሁለት በመቶው ደም ሲለግስ ነው። ይሁን እንጂ በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለው የደም መለገስ ባሕል ዝቅተኛ በመኾኑ በ2015 ዓ.ም በ11 ወር ውስጥ በሀገሪቱ የተሰበሰበው ደም 320 ሺህ ዩኒት ብቻ ነው። ከዚህ ውስጥ 100 ሺህ ዩኒት ደም የተሰበሰበው በብሔራዊ ደም ባንክ ሲኾን 78 ሺህ ዩኒት ደም ደግሞ በአማራ ክልል ከሚገኙ 10 የደም ባንኮች የተሰበሰበ ነው። በአማራ ክልል የተሰበሰበው ደም አጠቃላይ ከሀገሪቱ ከተሰበሰበው 26 በመቶ ይሸፍናል። በሀገሪቱም አንደኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
የሀገሪቱን የደም ምርመራ ሥርዓት ለማዘመን የፌዴራል መንግሥት ሰባት ደም ባንኮች የ”አውቶሜሽን ማሽን” ምርመራ እንዲጀምሩ ማድረጉን ገልጸዋል። ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ የባሕርዳር ደም ባንክ አንዱ መኾኑን አንስተዋል። ከዚህም በተጨማሪ የደም መቅጃ ከረጢቶችን፣ የመመርመሪያ ኪቶችን የመሳሰሉ የምርመራ ግብዓቶችን እያቀረቡ መኾኑን ገልጸዋል።
ደም መለገስ የታካሚዎችን ሕይወት ከመታደግ ባለፈ ለጋሾቹን ለተለያዩ በሽታዎች ተጋላጭ መኾናቸውና አለመኾናቸውን ምርመራ እንዲያደርጉና ችግር ካለም በፍጥነት ሕክምና እንዲያገኙ ያደርጋል።
ደም በመደበኛነት የሚለግሱ ሰዎች አጋጣሚ በኾነ የልብ ሕመም የመሞት አጋጣሚን እስከ 80 በመቶ ይቀንሳል። በመኾኑም ደም በመደበኛነት መለገስ ከልብ፣ ከጉበት፣ ከጣፊያ፣ ከካንሰር በሽታ ተጋላጭነት ይከላከላል። አንድ ሰው በተደጋጋሚ ደም የሚለግስ ከኾነ የደም ሴሎቹ የሚመነጩበት መቅኒ አዳዲስ የደም ሕዋሳት ስለሚያመነጩ ጤናማ ሰውነት እንዲኖረው ያደርጋል። ክብደት ለመቀነስም ይጠቅማል።
በለገስነው ደም የሰው ሕይወት ሲተርፍ ደስተኛ እና ጤናማ እንድንኾንም ያደርጋል።
የሚለገሰውም ለማንኛውም ደም ለሚያስፈልገው ሰው ሕክምና ስለሚውል ማኅበራዊ ትስስርን በመፍጠር ጥቅሙ የጎላ በመኾኑ ደም በመለገስ በደም መፈሰስ ሕይወታቸውን ሊያጡ የሚችሉ ወገኖችን መታደግ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!