
ባሕር ዳር: ሰኔ 13/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በደራ፣ ፎገራና ሊቦ ከምከም ወረዳዎች ሊከሰት የሚችለውን የጎርፍ አደጋ ለመከላከል የሚያስችል ሥራ መሠራቱን የደቡብ ጎንደር ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ገልጿል። በአማራ ክልል የጎርፍ አደጋ ከሚከሰትባቸው አካባቢዎች የፎገራ ወረዳ አንዱ ነው። በወረዳው በተለይም ደግሞ በ2012 ዓ.ም በተከሰተው ጎርፍ ከ15 ሺህ 400 በላይ ሰዎች መፈናቀላቸው ይታወሳል። ከ 6 ሺህ 800 በላይ ሄክታር መሬት ሰብል የወደመበት ወቅትም ነበር።
በ2013 እና 2014 ዓ.ም የጎርፍ መከላከል ሥራ በመሠራቱ ጉዳቱ መቀነሱን በፎገራ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት የቅድሚያ ማስጠንቀቂያና ፈጣን ምላሽ ቡድን መሪ ሙሉነሽ አስረስ ነግረውናል። በዚህ ዓመትም በ 2 ሚሊዮን ብር በርብ እና ጉማራ ወንዞች 5 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የጎርፍ መከላከያ ክትር ሥራ መሠራቱን ገልጸዋል። ከዚህ በተጨማሪ በማኅበረሰቡ ተሳትፎ ጎርፍ ሰብሮ ሊወጣ የሚችልባቸውን ቦታዎች የመከተር ሥራ ተሠርቷል። በየዓመቱ የሚከሰተውን ጎርፍ ለመከላከል ዘላቂ የጎርፍ መከላከያ ሥራ ላይ ማተኮር እንደሚገባም ነው ባለሙያዋ ያነሱት።
የደቡብ ጎንደር ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት የቅድሚያ ማስጠንቀቂያና ፈጣን ምላሽ ቡድን መሪ ስዩም አስማረ እንዳሉት ርብ፣ ጉማራና ሌሎችም ወንዞች ከመጠን በላይ መሙላትና የጣና ሀይቅ ከነበረበት መጠኑ በመስፋቱ ምክንያት በደራ፣ ፎገራና ሊቦ ከምከም ወረዳዎች ከፍተኛ ጉዳት ሲያደርሱ ቆይተዋል።
በተለይም ደግሞ በ2012 ዓ.ም በነበረው ከፍተኛ የዝናብ ስርጭት እና የጎርፍ አደጋ መከላከያ ክትር ባለመሠራቱ በደረሰው የጎርፍ አደጋ በማኅበረሰቡ ሀብትና ንብረት ላይም ጉዳት ደርሷል። ይሁን እንጅ በ2013 እና በ2014 ዓ.ም የተለያዩ የጎርፍ መከላከል ሥራዎች በመሠራቱ ችግሩን መቀነስ ተችሏል። በዚህ ዓመትም ከዚህ በፊት ተሠርተው በደለል የተሞሉና ሰብሮ ሊወጣ የሚችልባቸውን ቦታዎች ክልሉ በመደበው ከ 7 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር በጀትና በማኅበረሰቡ ተሳትፎ ደለል የማውጣት እና በወንዙ ግራና ቀኝ የመከተር ሥራ መሠራቱን ገልጸዋል።
በየዓመቱ የደለል ማውጣት ሥራ ከመሥራት ባለፈ ዘላቂ የክትር ሥራ በመሥራት የሚከሰተውን የጎርፍ አደጋ መከላከል እንዲቻልም ጠይቀዋል። በቀጣይ ጎርፍ የሚከሰት ከኾነ ማኅበረሰቡ ቀድሞ እንስሳትን ወደ ከፍተኛ ቦታ የማውጣት ሥራ እንዲሠራ አሳስበዋል። ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤቱም ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!