
ባሕር ዳር: ሰኔ 13/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ኀብረተሰብ ጤና ኢኒስትቲዩት በክረምት የሚከሰቱ ተላላፊ በሽታዎችን አስመልክቶ የጥንቃቄ መልዕክቶችን አስተላልፏል። የአማራ ክልል ኀብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ ክረምቱን ተከትሎ በሚከሰቱ ተላላፊ በሽታዎች ጉዳት እንዳይደርስ ቅድመ ዝግጅት መደረጉንም ጠቁመዋል፡፡ የኀብረተሰብ ጤና አደጋን ለመከላከል ትኩረት ተሠጥቶ እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል፡፡
አቶ በላይ የችግር ቀጣናዎች ተብለው የተለዩ ዞኖች ያሉ ቢኾንም የየአካባቢው መሥተዳደር ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው ብለዋል፡፡ ችግሩ በመጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ተፈናቃዮች ላይ ጉዳት እንዳያደርስም ከምግብ እና ከመጠጥ ጋር የተያያዙ ስጋቶችን መለየት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ችግሮች እንዳይከሠቱ አስቀድሞ ለመከላከልም እየተሠራ መኾኑን ነው የተናገሩት። ኢኒስቲትዩቱ ካሁን በፊት የነበሩ እቅዶችን በመከለስ ሊፈጠር የሚችለውን አደጋ ለመቀነስ እየሠራ ነው ብለዋል፡፡ በክረምት ሊከሰቱ የሚችሉ ተላላፊ በሽታዎችን ኀብረተሠቡ እንዲከላከል እና እንዲቆጣጠር የሚመለከታቸው አካላት ዕውቅና የመፍጠር ሥራ እንዲሠሩም አሳስበዋል፡፡ በተለይ ተፈናቃዮች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ አስቀድመው እየሠሩ መኾኑን ነው አቶ በላይ የገለጹት፡፡ በጎርፍ እና በሌሎች ችግሮች ሊከሰቱ የሚችሉ ተላላፊ በሽታዎችን ለመቆጣጠር ጥረት መደረግ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
የአማራ ክልል ኀብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት የኀብረተሰብ ጤና አደጋዎች መከላከል እና መቆጣጣር ዳይሬክተር አብርሃም አምሳሉ በበኩላቸው የወባ በሽታ በክልል እየጨመረ መኾኑን ጠቁመዋል፡፡ አቶ አብርሃም ከተለያዩ ክልሎች የሚመጡ የቀን ሠራተኞች በ11 የልማት ቀጣናዎች እየሠሩ ነው፡፡ እነዚህን ሠራተኞች ከበሽታ ለመቆጣጠር ኢኒስቲትዩቱ እየሠራ መኾኑንም አንስተዋል፡፡
ኀብረተሠቡ የተጠራቀሙ ውኃዎችን በማፋሰስ እና በማዳፈን ወባን የመከላከል ሥራውን አጠንክሮ እንዲሠራ ጠይቀዋል፡፡ በክልል 28 ወረዳዎች ላይ አጎበር ለማሰራጨት እየተሠራ መኾኑንም አስረድተዋል፡፡ ማኅበረሰቡ የአካባቢ ቁጥጥር ሥራውን አጠናክሮ መቀጠል አለበት ነዉ ያሉት፡፡ በተለይ የውኃ ተቋማት እንዳይበከሉ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ኢኒስትቲዩቱም ቅድመ ዝግጅቱን አጠናቅቆ ወደ ተግባር ምዕራፍ መግባቱንም አንስተዋል አቶ አብርሃም፡፡
ዘጋቢ ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!