ከረጅም ጊዜ በኋላ ወደ ቀያቸው የተመለሱ ወገኖች ድጋፍ እንዲደረግላቸው ተጠየቀ፡፡

83

ባሕር ዳር: ሰኔ 13/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በዋግኸምራ ብሔረስብ አሥተዳደር ከመጠለያ ወደ ቀያቸው የተመለሱ ወገኖች ድጋፍ እንዲደረግላቸው ተጠይቋል፡፡

በነበረው የወረራ ጦርነት ሕይዎት ጠፍቷል፣ ሀብትና ንብረታቸውን አጥተዋል፤ ከቀያቸውም ተፈናቅለው ኖረዋል፡፡

በዋግኸምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር በሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖች ከሞቀ ቤታቸው ተፈናቅለው በመጠለያ ውስጥ ሕይዎትን ሲገፉ ቆይተዋል፡፡ ከረጅም ጊዜ በኋላ በተሠራው ሥራ በመጠለያ የነበሩ ወገኖች ወደ ቀያቸው ተመልሰዋል፡፡ ለረጅም ጊዜ በመጠለያ ቆይተው ወደ ቀያቸው የተመለሱ ወገኖችም ሃብት አፍርተው ራሳቸውን እስኪችሉ ድረስ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል፡፡

ወይዘሮ አየሁሽ ወልዴ ከሞቀ ቤታቸው ተፈናቅለው ለሁለት ዓመታት በመጠለያ ውስጥ ቆይተዋል፡፡ አሁን ላይ ደግሞ ሲናፍቋት ወደቆየችው ቀያቸው ተመልሰዋል፡፡ ወደ ቀያቸው በመመለሳቸውም ደስተኛ መኾናቸውን ነግረውኛል፡፡ ነገር ግን ወደ ቀያቸው ሲመለሱ ቤታቸው ተዘርፎ፣ ባዶውን በማግኘታቸው ችግር ውስጥ መውደቃቸውን ነው የገለጹት፡፡

ወደ ቤታችን በመግባታችን ተመስገን ብንልም ድጋፍ ግን እየተደረገልን አይደለም ነው ያሉት፡፡ የድጋፉ መቅረት ለችግር እንደዳረጋቸውም አስታውቀዋል፡፡ ከእለት ጉርስ ባለፈ የጤና አገልግሎት እንደሚያስፈልጋቸውም ነግረውኛል፡፡ የቤት እቃና ሌሎች መገልገያዎች እንደሚያስፈልጓቸውም ገልጸዋል፤ ከሁሉም በላይ ግን ቀለብ ለነገ የሚባል አይደለም ነው ያሉት፡፡

የዋግኸምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ምህረት መላኩ ከሁለት ወረዳዎች ተፈናቅለው በመጠለያ ጣብያ ውስጥ የነበሩ ወገኖች ወደቀያቸው መመለሳቸውን ተናግረዋል፡፡ ወደ ቀያቸው ከተመለሱ በኋላ አንድ ዙር ድጋፍ ማሰራጨታቸውንም አስታውቀዋል፡፡ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉ እየሠሩ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡

አካባቢው የጦር ቀጣና ኾኖ ስለቆየ ቤትና ንብረት መውደሙን ያነሱት ኀላፊው ተፈናቅለው የነበሩት ብቻ ሳይኾን በቀያቸው ኾነው በጦርነት ውስጥ የነበሩ ወገኖችም ድጋፍ ይሻሉ ነው ያሉት፡፡ በጦርነት ውስጥ ለነበሩትና በችግር ውስጥ ላሉት ወገኖች ድጋፍ ማድረግ አለመቻላቸውንም አስታውቀዋል፡፡ የእንስሳት ግዢ፣ የዘር እና የቤት ውስጥ ቁሳቁስ ድጋፍ እንዲደረግ ጥረት እያደረጉ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡ አርሶ አደሮች የዘር ወቅት ሳያልፍ ዘርተው በሚቀጥለው ዓመት ራሳቸውን እንዲችሉ ለማድረግ ጥረቶች መኖራቸውንም አስታውቀዋል፡፡

በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ወደ መልሶ ግንባታ ሥራ የገባ ግብረ ሰናይ ድርጅት አለመኖሩንም ገልጸዋል፡፡ ወደ ቀያቸው የተመለሱ ወገኖች የሚያነሱት ጥያቄ ትክክል መኾኑንም አንስተዋል፡፡ ለረጅም ጊዜ በጦርነት ውስጥ ለቆዩ አካባቢዎች ለሁሉም ሕዝብ ድጋፍ ሊደረግለት ይገባልም ነው ያሉት፡፡ እስካሁን ድረስ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ሁሉ ድጋፍ ማድረግ አለመቻላቸውንም ገልጸዋል፡፡

መንግሥት፣ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች እና ግለሰቦች ተፈናቅለው የቆዩ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም ርብርብ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ብሔረሰብ አሥተዳደሩ የወደሙ ሃብቶችን እያጠኑ የሚያስፈልገውን ድጋፍ እየለዩ መኾናቸውንም አስታውሰዋል፡፡

የአማራ ክልል አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋሰትና ኮሚሽን ኮሚሽነር ዲያቆን ተስፋው ባታብል በመንግሥት እና በረጅ ድርጅቶች አማካኝነት እርዳታ ሲደረግ መቆየቱን ተናግረዋል። ከተፈናቃዮች ባለፈ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ ወገኖች የኑሮ ልየታ እየተሠራ ድጋፍ እንደሚደረግም አንስተዋል። እርዳታው አሁንም እየተሰጠ መኾኑንም ገልጸዋል።

ዩ.ኤስ.ኤ.አይ.ዲ እርዳታ ማቆሙን ያስታወሱት ኮሚሽነሩ እርዳታ ማቆሙ ከፍተኛ ጫና መፍጠሩንም ተናግረዋል። በዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር 67 ሺህ የሚኾኑ ወገኖች ወደቀያቸው መመለሳቸውንም ገልጸዋል።

የዓለም አቀፉ ድርጅቶች እርዳታ ካልተጠናከረ በስተቀር በእኛ አቅም አንችለውም ብለዋል። የክልሉ መንግሥት ባለው አቅም ልክ ድጋፍ እያደረገ መኾኑን ያነሱት ኮሚሽነሩ ካለው የተፈናቃይ እና ተመላሽ ቁጥር አንፃር ድጋፍ ለማድረግ አስቸጋሪ እንደሚኾንም ነው የተናገሩት። ለእርዳታ የሚቀርብ እህል ገበያ ላይ እንዳይሸጥ፣ እንዳይሰረቅና ለአልተገባ ሰው እንዳይሰጥ ብርቱ ክትትል እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል። እርዳታዎች በተገቢው መንገድ ለተጠቃሚው ኅብረተሰብ እንዲደርሱ እየሠሩ መኾናቸውንም አስታውቀዋል። ከሚደረገው ድጋፍ ባለፈ በየአካባቢው ሃብት የማሰባሰብ ሥራ እንሠራለንም ብለዋል።

ካለው የኑሮ ውድነት አንፃር መንግሥት ብቻውን ሊቋቋመው እንደማይችልም አመላክተዋል። የክልሉ መንግሥት ፕሮጄክቶችን እየተወ ድጋፍ እያደረገ መኾኑንም ገልጸዋል። ሁሉም ለተፈናቃይ ወገኖች ድጋፍ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል።

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሕገ-ወጥነት በክልሉ የገቢ አሰባሰብ ሥራ ላይ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ እያደረሰ ነው” ገቢዎች ቢሮ
Next articleየፈተና ጥሪ ማስታወቂያ