
ባሕር ዳር: ሰኔ 13/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የገቢ ግብር አሰባሰብ ሥራ ላይ ሕገ-ወጥነት ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ እያደረሰ እንደኾነ የክልሉ ገቢዎች ቢሮ አስታውቋል።
በቢሮው የግብር፣ ትምህርትና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አግማስ ጫኔ እንደሚሉት ሐሰተኛ ደረሰኝ መጠቀም፣ ያለደረሰኝ ግብይት መፈጸም፣ ግብር ሥወራ፣ የአየር ባየር ንግድ/ ያለፈቃድ መነገድ ገቢ ሰብሳቢው ተቋም የሚገባውን እንዳይሰበስብ አድርጓል፣ መንግሥትንም ለኢኮኖሚያዊ ኪሳራ ዳርጓል ነው ያሉት።
በንግድ ዘርፉ 40 በመቶው የንግድ እንቅስቃሴ የሚፈጸመው በስውር በሚካሄድ ንግድ ስለመኾኑ ጥናት አመላክቷል ያሉት አቶ አግማስ ሕገወጦችን ሥርዓት ለማስያዝ እርምጃ እየተወስደ ነው ብለዋል።
ቢሮው ሕገወጦችን እየታገለ፣ ቀላልና ቀልጣፋ አሠራሮችን በማንበር የበጀት ዓመቱን እቅድ ለማሳካት እየሠራ እንደኾነም ነው ያስረዱት።
በ2015 በጀት ዓመት ከ42 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ መታቀዱን አንስተዋል።
እስከ ሰኔ 2/ 2015 ዓ.ም 33 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በመሰብሰብ የእቅዱን 77 ነጥብ 7 በመቶ መሰብሰብ ችሏል ነው ያሉት ዳይሬክተሩ።
ባሉት ቀሪ ጊዜያት እቅዱን ለማሳካት ጥረት ይደረጋል ያሉት አቶ አግማስ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ግን የተሻለ አፈጻጸም እንዳለው ገልጸዋል።
ይህ ዘገባ እስከተዘጋጀበት ጊዜ ድረስ የገቢ ግብር ከሰበሰባቸው ዘርፎች መካከል፦
👉 6 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ከቫት ተመዝጋቢዎች፣
👉6 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ከመንግሥት ሠራተኞች፣
👉4 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ከግል ተቀጣሪ ሠራተኞች፣
👉2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ከንግዱ ማኅበረሰብ የተሰበሰበ መኾኑንም ገልጸዋል።
በግብር አከፋፈል እቅድ የተሻለ አፈጻጸም ደረጃ ያሳዩ ከተሞች 102 ነጥብ 9 በመቶ በመፈጸም ወልዲያ ከተማ ቀዳሚነትን ሲይዝ ደብረታቦር ከተማ ደግሞ 101 ነጥብ 7 በመቶ በመፈጸም ሁለተኛ ደረጃን ይዟል ነው የተባለው።
በዞን ደረጃ ዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ቀዳሚ ሲኾን ሰሜን ወሎ ዞን ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ የተሻለ ግብር የሰበሰቡ ዞኖች ኾነዋል።
ዘጋቢ፦ጋሻው አደመ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!