
አዲስ አበባ: ሰኔ 13/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ብሔር፣ ሃይማኖትና ፖለቲካ ችግሩ በጉልህ ያጠነጠነባቸው ናቸው ብሏል ባለስልጣኑ።
የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን በማኅበራዊ ሚዲያ የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭት ሀገራዊ ሪፖርትን ይፋ አድርጓል።
የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዮናታን ተስፋዬ ብሔራዊ ጥቅምን የሚጎዱና ሀገራዊ አንድነትን የሚያናጉ የጥላቻ ንግግሮችና ሐሰተኛ መረጃዎች አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሰዋል ብለዋል።
ባለሥልጣኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር እያደረገ ሲኾን ከታኅሣሥ/2014 ዓ.ም እስከ ታኅሣሥ/2015 ዓ.ም የማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ባደረገው ክትትል ተመሥርቶ ያዘጋጀውን ሪፖርት ይፋ አድርጓል።
ሪፖርቱን ያቀረቡት የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የበይነ መረብ መገናኛ ብዙኃን ክትትልና አቅም ግንባታ ዳይሬክተር ኤደን አማረ ፌስቡክ፣ ቴሌግራም፣ ትዊተር፣ ቲክቶክና ዩቲዩብን በመጠቀም በብሔር ፣በሃይማኖት ፣በፖለቲከኞችና በሌሎች ታዋቂ ግለሰቦች ላይ የማዋረድ፣ የመነጠል፣ እና ስም የሚያጠለሹ ጉዳዮች ተበራክተዋል ብለዋል።
በዋነኝነትም ሕዝብን፣ ፖለቲከኞችን እና እንደ አጠቃላይ ሀገርን የሚመለከቱ እንደነበር ተገልጿል።
በቅርጽ፣ በይዘት፣ በዘዴ፣ በምንጭ፣ በመገለጫ፣ በዓላማና በዒላማ ተለይተው በማኅበራዊ ሚዲያዎች የሚታዩ ስርጭቶች እና ግኝቶች መኖራቸውም ተነግሯል።
የማኅበራዊ ሚዲያ አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች እርምጃ ሲወስዱ አለመታየቱም እንደ ችግሩ ማባባሻ ተወስዷል።
የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የስትራቴጂክ ጉዳዮች ዳይሬክተር ታምራት ደጀኔ ፖሊሲዎች፣ የሕግ ማዕቀፎች፣ ጥናትና ምርምሮች እንዲሁም የግንዛቤ መፍጠሪያ መድረኮች ሊዘጋጁ ይገባል የሚሉ ምክረ ሐሳቦችን አቅርበዋል።
ዘጋቢ፡- ድልነሳ መንግሥቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!