ኢትዮጵያ ከማላዊ ጋር የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዋን ዛሬ ታደርጋለች

91

ባሕር ዳር: ሰኔ 13/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ አምስተኛ የምድብ ጨዋታውን ዛሬ ከማላዊ አቻው ጋር ያከናውናል። የሁለቱ ሀገራት ጨዋታ በሞዛምፒክ ዚምፔቶ ብሔራዊ ስታዲየም ከቀኑ 11 ሰዓት ላይ ይደረጋል።

በኮትዲቭዋር አስተናጋጅነት እ.አ.አ በ2024 በሚካሄደው 34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለመሳተፍ በምድብ 4 የማጣሪያ ጨዋታውን እያደረገች ያለችው ኢትዮጵያ ከውድድሩ ውጪ መሆኗ ይታወቃል። ዋልያዎቹ በሶስት ነጥብ በምድቡ የመጨረሻውን አራተኛ ደረጃ ይዘዋል። በጊዜያዊ ዋና አሰልጣኝ ኢንስትራክተር ዳንኤል ገብረማርያም የሚመራው ብሔራዊ ቡድኑ ከማላዊ ጋር ላለበት ጨዋታ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ዝግጅት ሲያደርግ የቆየ ሲሆን ላለፉት ሁለት ቀናት በሞዛምቢክ ልምምዱን አድርጓል።

የዛሬው ጨዋታ ለዋልያዎቹ ከመርሐ-ግብር መሟያ ያለፈ ትርጉም የሌለው ጨዋታ ነው። እንደ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በጊዜያዊ አሰልጣኝ ፓትሪክ ማቤዲ የምትሰለጥነው ማላዊ በምድብ 4 በሶስት ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።
ነበልባሎቹ የሚል ቅጽል ስም ያላቸው ማላዊዎች ለጨዋታው በሀገር ቤት እና በሞዛምቢክ ዝግጅታቸውን አድርገዋል። ማላዊ በመጀመሪያው የምድብ ጨዋታ ኢትዮጵያን 2 ለ 1 ማሸነፏ የሚታወስ ነው።

በምድብ 4 ግብጽ በ12 ነጥብ ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፏን አረጋግጣለች። ጊኒ በ9ኝ ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዛለች። በኮትዲቭዋር አስተናጋጅነት እ.አ.አ በ2024 በሚካሄደው 34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ 24 ሀገራት ይሳተፋሉ።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleMaxxansa Gaazexaa Hirkoo, Waxabajjii 15/2015
Next articleቺርቤዋ ሴኒ 15 ጌርክ 2015 ምሬት አሜታ