
“መልሶ የማቋቋም እና ወደ ቀያቸው የመመለስ ሥራ በትኩረት እየተሠራ ነው” የአማራ ክልል አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋሰትና ኮሚሽን
ባሕር ዳር: ሰኔ 12/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ተኩለው የተዳሩበት፣ ልጆች ወልደው የሳሙበት፣ እሸት ቆርጠው የቃሙበት፣ ወተት አልበው የጠጡበት፣ ደግሰው ዘመድ አዝማድ የጠሩበት፣ የመሸበት ያሳደሩበት፣ የተጠማን ያጠጡበት፣ የተራበን ያጎረሱበት፣ የታረዘን ያለበሱበት፣ ወጭና ወራጁ የሚያርፍበት የሞቀ ቤታቸው ናፍቋቸዋል። ከብቶቻቸው የተሰማሩበት መስክ ፣ ልጆቻቸው የሚጫወቱበት ሥፍራ፣ የኖሩበት ቀያቸው ውል ብሏቸዋል።
በሚወዷት ሀገራቸው በደልና መከራ ጠናባቸው፣ ደጎች ሳሉ ክፉዎች አሳደዷቸው፣ ከሞቀ ቤታቸው አስወጥተው፣ ሀብትና ንብረታቸውን አሳጥተው የሰው እጅ አሳዩዋቸው። ከአፋቸው ክፉ የማይወጣው፣ እጃቸው ለመስጠት ብቻ የሚዘረጋው፣ አንጀታቸው ለፍጥረት ሁሉ የሚያዝነው፣ የሚራራው እኒያ ደገኛ ሰዎች መከራ ፀናባቸው።
አራሽ አንደፋራሽ፣ በችግር ቀን ደራሽ፣ አልባሽና አጉራሽ ኾነው ሳለ በደል ሳይገኝባቸው፣ ክፋት ሳይቆጠርባቸው ለችግር ተጋለጡ። አያሌ ደስታ ያሳለፉበት፣ ልጅ ድረው እልል ያሉበት፣ ዓመታትን በደስታ የኖሩበት ቤታቸው በነበር ቀርቷል። አርሰው፣ አንደፋርሰው እሸት የበሉባቸው በሬዎቻቸው፣ የበሬዎቻቸው ምትክ ብለው ዓይን ዓይን እያዩ ያሳደጓቸው ወይፈኖቻቸው፣ ወተት የሚሰጧቸው ላሞቻቸው፣ የላሞቻቸው ምትክ ይኾኑ ዘንድ በደስታ ያሳደጓቸው ጊደሮቻቸው፣ በግና ፍየሎቻቸው፣ ፈረስና በቅሎዎቻቸው ትናንት በዙሪያቸው የነበሩት ሃብቶቻቸው ሁሉ በትዝታ ቀርተዋል። ከመልካም ሕይወት ወጥተው የሰው እጅ እያዩ ካደሩ ጊዜያት ተቆጥረዋል።
ዋጋ ከፍለው ባፀኗት፣ እየሞቱ ባኖሯት፣ እየደሙ በጠበቋት፣ ከሕይወታቸው በላይ በሚወዷት ሀገራቸው መኖር ቸገራቸው። ክፉዎች አሳደዷቸው፣ ገፏዋቸው። ወዳጅ ዘመዶቻቸው በሞት አውታር ተይዘው ሲቃትቱ አይተዋል፣ የሚወዷቸውን ወዳጅ ዘመዶቻቸውን በግፍ ተነጥቀዋል።ያዩት መከራ ብዙ ነው። ይህ ሁሉ መከራ የበዛባቸው ያለ በደል ያለ ሐጥያት ነበር።
ኢብራሂም አሕመድ ይባላሉ። ከምዕራብ ወለጋ ተፈናቅለው በሐይቅ መጠለያ ጣቢያ ውስጥ ተጠልለው ይኖራሉ። እሳቸው ተወልደው ያደጉት በዚያው በወለጋ ነው። ተወልደው ባደጉበት፣ አድገው ወግ ማዕረግ ባዩበት ምድር ነገድ ተቆጥሮባቸው፣ ማንነት እንደበደል ታይቶባቸው ነገዳቸው ወደሚመዘዝበት ምድር ሂዱ ተባሉ። እኒህ የመከራ ገፈት ቀማሽ ሰው የስድስት ልጆች አባት ናቸው። በወለጋ ሲኖሩ የተሟላ ቤት እና ንብረት ነበራቸው። ነገዳቸው ተቆጥሮ ሲሳደዱ ግን አንድም ንብረት አልወጣላቸውም። ከእርሳቸው ጋር አብሮ የተሰደደው የወዳጅ የዘመዶቻቸው የግፍ ግድያ ትዝታና ስቆቃ ብቻ ነው። ለዓመታት ላብ ጠብ አድርገው የሠሩት ሁሉም በነበር ቀርቷል” የከተማና የገጠር ቤት ነበረኝ፣ ሃብቴ ሙሉ ነበር፣ ተፈናቅለን ስንመጣ ግን አንድም አልቀረም ሁሉም አመድ ኾኖ ነው የቀረው” ነው ያሉኝ።
ቤት ንብረታቸውን አጥተው፣ የሚወዷቸው ዘመዶቻቸውን በግፍ ሲገደሉ አይተው፣ ከሞት መንጋጋ ወጥተው፣ ቤት እየናፈቃቸው፣ ልጆቻቸው እያለቀሱባቸው በመጠለያ ውስጥ መኖር ከጀመሩ ሦስት ዓመታትን አስቆጥረዋል። “እንኳ ለራሳችን ለሰው እንተርፍ ነበር። አሁን ግን ሁሉም የለም። ሁሉም እዛው ቀርቷል” ነበር ያሉኝ። ሀገራችሁ አይደለም አሉን፣ ከዚህ ውጡ አሉን በማለት ያን ጊዜ ያስታውሱታል።
ከሞቀ ቤታቸው ወጥተው በመጠለያ ውስጥ እያሳለፉት ስላለው ሕይወት ሲናገሩ ” ከሞቱት ይሻላል፣ ሜዳ ለሜዳ የሞቱ አሉ። ከሞቱት እንሻላለን፣ ቢርበንም ቢጠማንም ሰላም አለ፣ ተኝተን እናድራለን፣ መንግሥትም ኾነ በጎ አድራጊው እየተባበረን አለን እስካሁን ረሃብ አልገደለንም” በማለት ሕይዎታቸው ከሞቱት በላይ ካሉት ደግሞ በታች መኾኑን ይገልጻሉ። የሚደረገው ድጋፍ ይቆራረጣል፣ ሲሰጥም በቂ አለመኾኑንም ነግረውኛል።
“መንግሥት የጠፋና የወደመ ንብረታችን እንዲያስመልስልን እንጠይቃለን፣ ወደ ቦታችን ተመልሰን ሠርተን መኖር እንፈልጋለን፣ ሁልጊዜ አሥራ አምስት ኪሎ ከምንቀበል እና የሰው እጅ ከማየት ሠርተን መብላት እንሻለን” ነው ያሉት።
ሌላኛው ከሁሩ ጉድሮ ወለጋ ተፈናቅለው የመጡት ገሰሰ አሻግሬ በመጠለያ ውስጥ መኖር ከጀመሩ ሦስት ዓመታት ተቆጥረዋል። እሳቸውም ተወልደው ያደጉት በዚያው በሁሩ ጉድሮ ወለጋ ነው። በዚያው ተወልደው ባደጉበት ሥፍራ ተድረው ተኩለው የሦስት ልጆች አባት ኾነዋል። በዚያ ሥፍራ ያርሳሉ ይነግዳሉ። እንደዛሬው ሳይኾን የተሟላ ቤትና ንብረት ነበራቸው። ተፈናቅለው ከመምጣታቸው አስቀድሞ ሸኔ ልጆቻቸውን በሚውሉበት እየሠረቀ ብር አምጡ እያለ ያስቸግራቸው እንደነበር ያስታውሳሉ። ከዚህም አለፍ ሲል ውጡ ወደ ሀገራችሁ ሂዱ እያሉ ያስፈራሯቸው ነበር። በመጨረሻ ግን በጅምላ መምታት ጀመሩ ሲሉ ነግረውኛል።
“ሕዝቡ ያለውን እያካፈለ እያኖረን ነው፣ ያን የጭንቅ ጊዜ እንድንረሳ የተቻላቸውን ያደርጋሉ” ብለውኛል። ከመከራ አትውጪ ያላት ነብስ ከወለጋ ተፈናቅለው መጥተው በመጠለያ በሚኖሩበት ጊዜም በሕወሃት ወረራ ጦርነት ተፈናቅለው ነበር። ያም ሕይወታቸውን በእጅጉ ፈትኖታል። አሁን ላይ ከመሞት የተሻለ ሕይወት ቢኖሩም በቂ የኾነ ድጋፍ እየተደረገላቸው አለመኾኑን ነግረውኛል።
ገሰሰ ተወልደው ወደ አደጉበት፣ ሃብትና ንብረት ወደ አፈሩበት ቀዬ መመለስ ይሻሉ። የሰላሙ ጉዳይ ግን ዋስትና እንደሚያሰፈልገውም ይናገራሉ፡፡ “መንግሥት ሰላሙን መልሶ ወደ ቀያችን ሊመልሰን ይገባል፣ በምንኖርበት አካባቢም የራሳችን ተወካይ ሊኖረን ይገባል፣ መንግሥት ዜጋዬ ናችሁ ካለ ደኅንነታችን ተጠብቆ በተወለድንበት ምድር መኖር እንፈልጋለን፤ ሰላሙን ካረጋገጠልን ወደ ቀያችን እንመለሳለን” ነው ያሉት።
እነዚህ ከማሳቸው የማይለዩ ብርቱ ገበሬዎች ዛሬ ላይ እጆቻቸው ሥራ ፈትተው፣ ሃብትና ንብረታቸውን አጥተው፣ የልጆቻቸውን መከፋት እያዩ የሰው እጅ ጠባቂ ኾነው ተቀምጠዋል። ከዚህ ሕይወት መውጣት እና ራሳቸው ሠርተው፣ አምርተው ለልጆቻቸው እንዳሻቸው ሲያደርጉ መኖር ደግሞ ፍላጎታቸው እና ሊያደርጉት የሚጓጉለት ነው።
የደቡብ ወሎ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽሕፈት ቤት የቅድመ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ቡድን መሪ መሐመድ ሰይድ በደቡብ ወሎ ዞን 46 ሺህ ከቀያቸው የተሳደዱ ወገኖች መኖራቸውን ገልጸዋል። አብዛኞቹ ደግሞ የመጡት ከኦሮሚያ ክልል መኾናቸውን ተናግረዋል።
ለተፈናቃይ ወገኖች ድጋፍ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑን የተናገሩት ቡድን መሪው ምግብ በበቂ ሁኔታ እየቀረበላቸው አለመኾኑንም አስታውቀዋል። በምግብ አቅርቦት ችግር ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች መኖራቸውንም ነግረውኛል። የሚደረገው ድጋፍ የተሟላ አይደለም ነው ያሉኝ።
የንፁሕ መጠጥ ውኃ አገልግሎት ችግር እንዳለባቸውም ተናግረዋል። ሁሉም ለተፈናቃዮች ልዩ ትኩረት በመስጠት ሊሠራ እንደሚገባም ገልጸዋል። ዋናው ሚናቸው በሕይዎት እንዲቆዩ ማድረግ እንደኾነም ተናግረዋል።
በአካባቢው ያሉ ባለሀብቶችን እያሳተፉ መኾናቸውንም ገልጸዋል። ካለባቸው ችግር አኳያ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ለእነዚያ አግኝተው ላጡ ወገኖች ሊደርስላቸው ግድ ይላል ነው ያሉት።
የአማራ ክልል አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋሰትና ኮሚሽን ኮሚሽነር ዲያቆን ተስፋው ባታብል በአማራ ክልል አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ተፈናቃይ ወገኖች መኖራቸውን ገልጸዋል። ተፈናቃዮቹ በመጠለያ ጣብያና በዘመድ አዝማድ እንደሚኖሩም ተናግረዋል። በመንግሥት እና በረጅ ድርጅቶች አማካኝነት እርዳታ እየተደረገ መኾኑንም አስታውቀዋል።
ከተፈናቃዮች ባለፈ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ ወገኖች የኑሮ ልየታ እየተሠራ ድጋፍ እንደሚደረግም አንስተዋል። እርዳታው አሁንም እየተሰጠ መኾኑንም ገልጸዋል። ዩኤስ አይዲ እርዳታ ማቆሙን ያስታወሱት ኮሚሽነሩ እርዳታ በማቆሙ ከፍተኛ ጫና መፍጠሩንም ተናግረዋል። የዓለም አቀፉ ድርጅቶች እርዳታ ካልተጠናከረ በስተቀር ችግሩ ሰፊ ነው ብለዋል።
የክልሉ መንግሥት ባለው አቅም ልክ ድጋፍ እያደረገ መኾኑን ያነሱት ኮሚሽነሩ ካለው የተፈናቃይ ቁጥር አንፃር ድጋፍ ለማድረግ አስቸጋሪ እንደሚኾንም ነው የገለጹት። በመጠለያ ውስጥ ለሚኖሩት ግን ቅድሚያ በመስጠት እየተከታተሉ ድጋፍ እንደሚያቀርቡም አስታውቀዋል። ሁሉም በሚችለው ልክ ድጋፍ እንዲያደርግም ጠይቀዋል።
ችግሮችን ለማቃለል ተፈናቃይ ወገኖችን ወደ ቀያቸው መመለስ እንደሚገባም ገልጸዋል። መሥራት የሚችሉ ወገኖች እንዲሠሩ የማድረግ ሥራ እየሠሩ መኾናቸውንም ተናግረዋል።
መልሶ የማቋቋም እና ወደ ቀያቸው የመመለስ ሥራ በክልሉ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል። ሁሉም ወገኖች ወደ ቀያቸው መመለስ አለባቸው ነው ያሉት። ወገኖችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ ደግሞ ብርቱ ሥራ ይጠይቃል ብለዋል።
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!