ከሥራ አጥ ቆጠራ የተሻገረ የሥራ እድል ፈጠራ ተግባር ያስፈልጋል!

136

ባሕር ዳር: ሰኔ 12/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ሥራና ሠራተኛው ተኳርፈው ጎዳና የለዩ ይመስላል፣ሥራ ፈላጊው ሥራ አጥቶ ያዛጋል፣ ሥራው የሚመጥነው ሠራተኛ ተቸግሮ አንጋጦ ያማትራል። አምራችነት ነጥፎ ገበያው ተርቦ ሸማችና ሻጭ ተፋጧል።

ገንዘብ ከመገበያያነቱ ስቶ ፣ከመሥሪያ መሳሪያነቱም ተኳርፎ የጥቂቶችን ካዝና ያሞቃል፣ ያደምቃል።

ገንዘብ ብዙዎቹ እጅ ላይ ሚዛን ስቷል።የፋይናንስ ተቋማትም ወጭና ገቢ እየቆጠሩ ‘ቆጥቡ’ ከማለት ባሻገር ‘ሥሩ’ የሚል ሃሳብና አስቻይ አሠራር ዘርግተው በሥራ እድል ፈጠራው ዘርፍ ለሁሉም ምቹ መደላድል መፍጠር አልተቻላቸውም።በዚህ ሁናቴ ታዲያ ሥራና ሠራተኛ አገናኙ አካል ፊደልና አሃዝ እያዋሃደ ኅልሙን ያወራል። ነዋሪውን የሚፈታተነው የኑሮ ውደነት መልኅቅ እንደሌለው መርከብ ነዋሪን በወጀብ ያናውጠዋል። አልሞት ባይ ተጋዳይ እጁን እየላሰ “እንዲህ ቢኾን ኖሮ እኮ እንዲህ ይኾን ነበር” እያለ አየር ይቀዝፋል።

ታዲያ የኢትዮጵያ የሥራ እድል ፈጠራ ‘ንቡራዊ’ መልክ የቱ ነው?

በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ሥራ ፈላጊዎች መኖራቸውን ይፋ ያደረገው የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በሚሊዮን ሥራ እድል እየፈጠረ ስለመኾኑም በሪፖርቱ ገልጿል።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እስከ 2017 ዓ.ም 14 ሚሊዮን ሥራ ፈላጊዎችን ባለሥራ የማድረግ እቅድ አለው። በተያዘው በጀት ዓመት ብቻ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ3 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ ለሚኾኑ ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር አቅዶ ከ2 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ለሚኾኑ ዜጎች የሥራ እድል እንደፈጠረም ነው ያሳወቀው። ውጤቱ ግን የሥራና ሠራተኛ ገበያውን ክፍተት አልሞላም ፣የሥራ አጡንም ጩኸት አላስታገሰም። አሁንም የሥራ ፈላጊው ቁጥር እልፍ ነው።
ለዓመታት ሥራ በመፈለግ ጊዜውን እና ጉልበቱን ያባከነው ወጣት ሞላ ወርቄ፤ የሥራ አጥነት ፈተና ከኢኮኖሚ እስከ ሞራል ኪሳራው ከባድ ብትር እንዳሳረፈበት ይናገራል።

‘ተምሮ ሥራ አጥነት’ የቤተሰብን ድካምና ተስፋ በከንቱ የሚያመክን፣ለተከታይ ታናናሽ እህት ወንድሞችም የመማር እድል መጥፎ ምሳሌነት ስለመኾኑም ነው የሚናገረው ወጣቱ።በእርግጥ ይህ አስተያየት የብዙዎች መሰል ሥራ ፈላጊዎችም ጭምር ነው። የግድ በተማርንበት ሙያ ተቀጣሪነትን አንሻም የሚለው ወጣቱ ሥራ ፈላጊ ሞላ ወርቄ ለመንግሥት አንድ ጥያቄ አለው” የመሥሪያ ገንዘብ አመቻችቶ የሥራ እድል የምንፈጥርበትን ቀላል፣ የሚደረስበት መንገድ ያዘጋጅ” ይላል። ቢሮክራሲ የበዛበት አሠራር ተጨማሪ መሰናክል ከመኾን በላይ መፍትሔ የለውም ነው የሚለው።

👉 ለሥራ እድል ፈጠራ የባለሙያዎች ምክረ ሃሳብ፦
በእርግጥም በኢትዮጵያ የሥራ እድል ፈጠራው ውስብስብ ችግሮች ላይ እንደወደቀ ነው የዘርፉ ባለሙያዎች የሚናገሩት።
ታዲያ እንዴት ከችግሩ ይታከም ጥያቄያችን ነው።

የሥራ እድል ፈጠራ ባለሙያው አቶ ይበልጣል ኤልያስ ፤ እንደሚሉት ለውስብስብ ችግር ቀላልና አንድ መፍትሔ ማምጣት ይቸግራል። ግን ደግሞ የሚያሠራ፣ የሚያስገድድ ፖሊሲ ነድፎ ማስተግበር ከመንግሥት የሚጠበቅ ግዴታ ነው ባይናቸው።

ችግሩ የሚጀምረው የትምህርት ሥርዓቱ ላይ እንደኾነ የሚናገሩት ባለሙያው ለገበያው የሚመጥን ተግባር ተኮር ሥልጠና በማዘጋጀት ብቁ የሰው ኀይል ማምረት ይገባል ነው የሚሉት።
አስተሳሰብና አመለካከት ላይ ተናቦ መሥራት፣ከግል ኢኮኖሚ አንቀሳቃሹ አካል ጋር ተቀናጅቶ መሥራት፣ የፋይናስ ተቋማት ትንንሽ የሥራ ዘርፎችና የወጣቶች የሥራ እድል ፈጣራን የሚያግዙበትን አስገዳጅ ፖሊሲና አሠራር በመዘርጋት ችግሩን ማከም ይቻላል የሰጡት ሙያዊ ማብራሪያ ነው።

በአንድ በኩል ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሥራ ፈላጊ መኖር የመንግሥት ችግር፣ በሌላ በኩል ደግሞ ዘመኑን የዋጀ ለገበያው የበቃ የሠለጠነ የሰው ኀይል አለማግኘት የኢንዱስትሪዎች ፈተና ስለመሆኑ ባለሙያዎቹ ይናገራሉ። በእርግጥ ይህ አገላለጽ በቀደሙ ዘገባዎቻችን የኢንዱስትሪ አሰሪዎች ያረጋገጡት ጉዳይ ነው። “የበቃ፣ የሰለጠነ የሰው ኀይል አጣን፣ ገበያውን የሞላው ተግባር ተኮር ሥልጠና የወሰደ ሳይኾን በንድፈ-ሃሳብ ትምህርት ሰልጥኖ የወጣ ሥራ ፈላጊ ነው” ከኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚሰነዘር ሃሳብ ነው።

በሀገር ደረጃ ባንኮች ዋና ትኩረታቸው ከፍ ላሉ ባለሃብቶች ማበደር እንጂ ትንንሽ የሥራ ዘርፎችና የወጣቶች የሥራ እድል ፈጣራን ከማገዝ አንጻር እዚግባ የሚባል ሚና እያሳዩ አይደለም ነው የባለሙያው አቶ ይበልጣል ግምገማ።
“ትልቅ ብር ለትንሽ ባለሃብት በማበደር ሀገርን በኢኮኖሚ ማሳደግ አይቻልም” ነው የሚሉት የሥራ እድል ፈጠራ ባለሙያው። ምንም የሥራ ዘርፉ ላይ ካልተቀላቀሉት እስከ ተደራጅተው ሥራን አሕዱ ካሉት የብድር አገልግሎት አቅርቦት ችግር በቀዳሚነት የሚነሳ ጉዳይ ነው።

👉 የብድር አቅርቦት ችግር :-
በባሕር ዳር ከተማ ተደራጅተው ሥራ የጀመሩት ትዕግስት፣ መሰለችና ጓደኞቻቸው የባልትና ውጤቶች የሽርክና ማኅበር የብድር አቅርቦት አለማግኘት አላሠራቸው እንዳለ ገልጸዋል። የማኅበሩ ሥራ አሥኪያጅ ትዕግስት ዓለሙ እንደሚሉት ማኅበሩ ምርቱን በስፋት ለገበያ ማቅረብ የሚያስችሉ ማሽኖች አሉት፣አምራች ሰራተኞችም አሉት በካፒታል እጥረት ግን ማስፋፋትም ኾነ የበለጠ ምርታማነት ላይ መሥራት አልተቻለም ይላሉ።ባንኮች የሚሰጡት ብድር “ላለው ይጨመርለታል” ነገር እንጂ ዝቅተኛ ሥራ ላይ የሚሠሩ አካላትን ያማካለ አይደለም አቤቱታቸው ነው።

👉 ሥራ የህልውና ጉዳይ:-
የሥራ እድል ፈጠራ ነገር ከኢኮኖሚያዊ እደገት ባሻገር በልቶ ማደርን ለማስቻል ብርቱ ሥራ የሚጠበቅበት ዘርፍ ኾኗል። የአማራ ክልል ሥራና ሥልጠና ቢሮ ምክትል ኀላፊ አወቀ ዘመነ የሥራ እድል ፈጠራ ጉዳይ የህልውና ጉዳይ እየኾነ ስለመምጣቱ ነው የሚናገሩት። እንደ አማራ ክልል ለሥራ እድል ፈጠራው ስኬታማነት ከአመለካከት አስከ አሠራር ያለውን መሰናክል ለመቅረፍ እየታገሉ ስለመኾኑም ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።
👉 የብድር አቅርቦትና ተጠቃሚነት በአማራ ክልል:-

በበጀት ዓመቱ 1 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ለማበደር ታቅዶ ከእቅድ በላይ 2 ነጥብ 4 ቢሊዮን የሚጠጋ ብር በፀደይ ባንክ በኩል ለሥራ እድል ፈጠራ ውሏል ነው ያሉት። በተጨማሪም የመመሪያ ማሻሻያ ተሠርቶለት እንዲፈጸም ከተደረገው ተዘዋዋሪ ፈንድ 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ብድር ተሰጥቷል ብለዋል። በድምሩ 3 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ለሥራ እድል ፈጠራ ብድር ውሏል ነው ያሉት ምክትል ቢሮ ኀላፊው።

በዚህም 76ሺህ 680 ሰዎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል። ይህ በኢንተርፕራይዝ ደረጃ ሲታይ 38ሺህ 148 መኾናቸውንም ነው የገለጹት። ክልሉ በዚህ ዓመት ብቻ 53ሺህ ኢንተርፕራይዞችን ማቋቋሙን ልብ ይሏል።

👉 የሥራ ፈላጊው ቁጥርና የተፈጠረው የሥራ እድል:-

በአማራ ክልል በበጀት ዓመቱ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ 1 ነጥብ2 ሚሊዮን በላይ የሥራ ፈላጊዎች ቁጥር ተመዝግቧል።

ከዚህም ከ867ሺህ በላይ ለኾኑት ዜጎች የሥራ እድር ተፈጥሯል ይላል ቢሮው። የብድር አገልግሎት ማግኘት የቻሉት ግን 76ሺህ የሚኾኑት ብቻ ናቸው ተብሏል።

ምክትል ቢሮ ኀላፊው አወቀ ዘመነ እንዳሉት ቅንጅታዊ አሠራርን የሚሻው የሥራ እድል ፈጠራ በተቋማት በኩል ዘርፉን ተቀናጅቶ ለማስተግበርና ችግሮችን ለመፍታት የአሠራር ደንብ ወጥቶ እየተተገበረ ነው ብለዋል።

የብድር አቅርቦት ፈተናውን ለመቅረፍም ባንኮች በአስገዳጅነት ለሥራ እድል ፈጠራው ለወጣቶች ማበደር የሚችሉበትን አሠራር አንዲከተሉ ከብሔራዊ ባንክ ጋር ንግግር እየተደረገ ነው ብለዋል።

ያምተባለ ይህ የሥራ እድል ፈጠራው ውስብስብ ችግሮችን ተሻግሮ መገኘት ይጠበቅበታል።

ዘርፉ ከሥራ አጥ ቆጠራ የተሻገረ የሥራ እድል ፈጠራ ተግባር ያስፈልገዋል።

ለዚህም ባለሙያዎች እንደሚሉት ተናባቢ ተግባር ያስፈልጋል።

ቀጣሪ ተቋማት ፣የትምህርት ተቋማት፣ምሩቃን(ሥራ ፈላጊዎች)፣ወላጆች፣ የፋይናንስ ተቋማትና መንግሥት ካልተናበቡ ለሥራ እድል ፈጠራው ችግር መፍትሔ የማይደረስበት ይኾናል።

በጋሻው አደመ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአሠልጣኝ ውበቱ አባተ የፋሲል ከነማ አሰልጣኝ ለመኾን ተስማማ
Next article“ወደ ቦታችን ተመልሰን ሠርተን መኖር እንፈልጋለን” ተፈናቃይ ወገኖች