
ባሕር ዳር: ሰኔ 12/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በክልሉ ስምንት ዞኖች የወባ የሕሙማን ቁጥር እየጨመረ እንደሚገኝ ተገልጿል። የወባ መድኃኒት እጥረት እና የኬሚካል ርጭት አለመደረጉ ለወባ በሽታ ሕሙማን ቁጥር መጨመር እንደ አንድ ምክንያት ተነስቷል፡፡
የአበርገሌ ወረዳ ነዋሪ አየሁሽ ወልዴ እንዳሉት የአልጋ አጎበር ተጠቃሚ ቢኾኑም ባለፉት ሁለት ዓመታት የኬሚካል ርጭት ባለመደረጉ የወባ ተጠቂዎች ቁጥር እየጨመረ ይገኛል፡፡ የወባ ሕሙማን ቁጥር ከመጨመሩ የተነሳ በጤና ተቋማት ሕክምና ለማግኘት መጨናነቅ መፈጠሩን አንስተዋል፡፡ ምርመራ ማድረግ የቻሉትም መድኃኒት እንደማያገኙ ነው ያነሱት፡፡ በጤና ተቋማት መድኃኒት እንዲሟላ እና በአስቸኳይ የኬሚካል ርጭት እንዲካሔድ ጠይቀዋል፡፡
በአበርገሌ ወረዳ የንየረ-አቁ ጤና አጠባበቅ ኀላፊ ታደሰ ከስኑ እንዳሉት በጤና ጣብያው የወባ ሕሙማን ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ይገኛል፡፡ በቀን በአማካይ የወባ ምርመራ ከሚያደርጉት 150 ሰዎች ውስጥ 100 ሰዎች በወባ ተጠቂ ናቸው፡፡ ከባለፉት ወቅቶችም በእጥፉ መጨመሩን ነው ያነሱት፡፡ በተቋማት የመድኃኒት እጥረት መኖሩ ደግሞ ጉዳዩን አሳሳቢ እንዳደረገው አንስተዋል፡፡
ለዚህ ደግሞ ባለፉት ሁለት ዓመታት በጦርነት ምክንያት የተቋረጠው ኬሚካል ርጭት አሁንም ድረስ አለመደረጉ ለመስፋፋቱ ምክንያት እንደኾነ አንስተዋል፡፡ በማኅበረሰቡ ተሳትፎ የማፋሰስ እና የማዳፈን ሥራ እየተሠራ መኾኑን የገለጹት ኀላፊው መንግሥት በፍጥነት የኬሚካል የርጭት እና የወባ መድኃኒት እንዲያቀርብ ጠይቀዋል፡፡
በክልሉ ከሐምሌ/2014 እስከ ሰኔ አጋማሽ 2015 ዓ.ም ከ998 ሺህ 600 በላይ የወባ ሕሙማን ሕክምና ማግኘታቸውን የአማራ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የወባ ፕሮግራም አስተባባሪ ዳምጤ ይላቅ ገልጸዋል፡፡ አስተባባሪው እንዳሉት በክልሉ ስምንት ዞኖች የሕሙማን ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ይገኛል። በሳምንት ብቻ ከ4 ሺህ በላይ የወባ ሕሙማን ጭማሪ ማሳየቱን ለአብነት አንስተዋል። ከዚህ ውስጥ ደግሞ ደቡብ ጎንደር፣ ምዕራብ ጎጃም፣ ማዕከላዊ ጎንደር፣ አዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር እና ባሕርዳር ከተማ ቀዳሚዎቹ ናቸው፡፡
የወቅቱ የዝናብ እና ሲፈስሱ የነበሩ ወንዞች መቆራረጥ፣ ማኅበረሰቡ የአካባቢ ቁጥጥር ሥራን ወጥ በኾነ መንገድ አለመሥራት፣ አጎበር በአግባቡ አለመጠቀም እና የማሰራጫ ጊዜ መራዘም እና የአየር ንብረት መቀያየር ለወባ መጨመር በምክንያትነት ተቀምጧል።
አስተባባሪው እንዳሉት ኢንስቲትዩቱ ወባን ለመከላከል በ82 ወረዳዎች አጎበር አሰራጭቷል፤ በክልሉ ርጭት ለሚያስፈልጋቸው 594 ቀበሌዎች የኬሚካል አቅርቦት እንዲደረግ ለጤና ሚኒስቴር ጥያቄ ቀርቧል፤ የርጭት ኬሚካሉ እስኪደርስ ሥልጠና እየሰጡ ይገኛል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ ለአንድ ወር እጥረት አጋጥሞ የነበረው የቫይቫክስ ወባ መድኃኒት በክልሉ መድኃኒት አቅራቢ ድርጅቶች መግባቱን ገልጸዋል፡፡ ሥርጭትም እንደሚካሄድ አንስተዋል።
የወባ በሽታን ለመከላከል ማኅበረሰቡ፡-
👉 የተሠራጨውን የመኝታ አጎበር በአግባቡ መጠቀም፣ እጥረቱ እንኳ ቢኖር ለሕፃናትና ለሚያጠቡ እናቶች ቅድሚያ መስጠት
👉 የአካባቢ ቁጥጥር ሥራ መሥራት እና የወባ መራቢያ ቦታዎችን ማፋሰስ፣ ማዳፈን
👉 ሙቀት፣ የራስ ምታት፣ መገጣጠሚያን መቆረጣጠም፣ ብርድ ብርድ ማለት፣ ማቅለሽለሽ ምልክቶች ከታዩ ፈጥኖ በአቅራቢያው በሚገኝ የጤና ተቋም በመሄድ ምርመራ ማድረግ
👉 ወባ ተገኝቶበት መድኃኒት የጀመረ ሰው መድኃኒቱን በአግባቡ መውሰድ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የአማራ ክልል 80 በመቶ ወባማ አካባቢ ሲኾን 68 በመቶ የማኅበረሰብ ክፍል ደግሞ ለወባ ተጋላጭ እንደኾነ የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት መረጃ ያሳያል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!