“ዓለም አቀፍ የውኃ ሥምምነቶች በተገቢው መንገድ አልተያዙም፤ የሚሻለው ትብብር እና በጎ ፈቃድ ነው” ፕሮፌሰር ሻፊቁል ኢስላም

30

ባሕር ዳር: ሰኔ 12/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የዓባይ ውኃ የዓለማችን ወቅታዊ የፖለቲካ እና የዲፕሎማሲ መነጋገሪያ አጀንዳ ነው፡፡ የውኃ ምርምር ማዕከላት እና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በወንዙ ውኃ ፍትሐዊ አጠቃቀም ዙሪያ በርካታ ጉዳዮችን ቢያነሱም ዘላቂ መፍትሔ ግን ያገኙለት አይመስልም፡፡ የዓባይ ውኃ ውዝግብ ለሺህ ዘመናት የዘለቀ ቢኾንም ቅኝ ገዥዎች እግራቸው አህጉሪቷን ከረገጠበት ወቅት ጀምሮ ደግሞ የበለጠ የሴራ ማዕከል እንዲኾን ተደርጓል የሚሉት ብዙ ናቸው፡፡

ከተፋሰሱ ሀገራት በላይ ቅኝ ገዥዎች ለዘመናት እንዳሻቸው የዘወሩት የዓባይ ውኃ አሁንም ድረስ የውኃው ባለቤት ሀገራት ባይተዋር የኾኑበት ቀደምት ሥምምነቶች እንደማጣቀሻ ሲነሱ ይስተዋላል፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ ክረምት ብቅ ባለ ቁጥር የዓባይ ውኃ ፖለቲካ አራማጆች እንደ ጎርፍ ይጠለቀለቃሉ፡፡ ፍትሕ እና ፍቅር፤ ትብብር እና ምክክር በሚሻው የዓባይ ውኃ አጠቃቀም ዙሪያ የተሳሳተ መንገድ እና ትርክት ተጠቂ የኾኑ ኀይሎች ተፈጥሯዊውን መብት ሲገዳደሩ መመልከት የተለመደ ኾኗል፡፡

በዓባይ ወንዝ የውኃ መጠን ከ85 በመቶ በላይ ድርሻ ያላት ኢትዮጵያ በወንዙ ያላት ተጠቃሚነት እስከ ቅርብ ዓመታት ድረስ ምንም የሚባል ነበር፡፡ ኢትዮጵያ እንደ ምዕራባዊያኑ የዘመን ስሌት 2011 ላይ በዓባይ ወንዝ ላይ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክትን ይፋ ስታደርግ ከተፋሰሱ ሀገራት በላይ ዓለም አቀፍ ጫናው እና ሙግቱ ብርቱ ኾኖ ብቅ አለ፡፡ በግልጽ እና ስውር መንገድ ካይሮ የምታስተባብረው የዓባይ ውኃ ሙግት የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት ሰለባ ኾኖ ተስተዋለ፡፡

የዓባይ ወንዝ ውኃ አጠቃቀም ፍትሐዊነት ከተፋሰሱ ሀገራት እና ከአህጉራዊው ድርጅት ወጥቶ ከተመድ የፀጥታው ምክር ቤት እስከ አውሮፓ ኅብረት፤ ከዓረብ ሊግ እስከ አሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ድረስ ለዓመታት መነጋገሪያ ርእሰ ጉዳይ ኾነ፡፡

አስታራቂዎቹም፤ ሕግ አርቃቂዎቹም በመልካዓ ምድራዊ አቀማመጥ እና በሥነ-ልቦና ከባለቤቶቹ የራቁ በኾኑበት ድርድር መላ ያጣው ሙግት ተመልሶ ወደ አህጉሩ ቢመጣም ከቅኝ ግዛት ሥነ-ልቦና ፈጽሞ ያልተላቀቁት የታችኛው የተፋሰሱ አንዳንድ ሀገራት ምክክሩን ስኬታማ እንዳይኾን ጫና ሲፈጥሩ ተስተውሏል፡፡

በአሜሪካ ቦስተን በታፍትስ ዩኒቨርሲቲ የውኃ ዲፕሎማሲ ዳይሬክተር፤ የፍሌቸር ሕግ እና ዲፕሎማሲ ትምህርት ቤት የሲቪል እና የአካባቢ ምህንድስና ፕሮፌሰር ሻፊቁል ኢስላም “ዓለም አቀፍ የውኃ ሥምምነቶች በተገቢው መንገድ አልተያዙም፤ የሚሻለው ትብብር እና በጎ ፈቃድ ነው” ሲሉ ይሞግታሉ፡፡ ፕሮፌሰሩ በሰጡት ሰፊ ትንታኔ በተለይም በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ እየተካሄደ ካለው ንግግር አንፃር የትብብር እና የንግግር በጎ አመለካከት እጅግ ጠቃሚ ጽንሰ ሀሳብ ነው ብለዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት የሀገሪቱን ዘላቂ የምጣኔ ሀብታዊ ልማት እና የኀይል ፍላጎት የሚመልስ ፕሮጀክት ነው የሚሉት ፕሮፌሰር ሻፊቁል ኢስላም ነገር ግን የኢትዮጵያ ጥረት ከተፋሰሱ የታችኛው ሀገራት በተለይም ከግብጽ ጋር ከፍተኛ ውጥረት ፈጥሯል ይላሉ፡፡ ሦስቱ ሀገራት ኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን 2015 ላይ በመርህ ደረጃ ስምምነት ተፈራርመው እንደነበርም አንስተዋል፡፡ ሥምምነቱ ትብብር እና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን የሚያጸና እንደነበር የሚያነሱት ፕሮፌሰር ኢስላም ከዚህ የሥምምነት መንፈስ የተሻለ አማራጭ አይኖርም ይላሉ፡፡

ግብጽ የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሂደት እና የውኃ ሙሌትን ለመቆጣጠር የሚያስችላት አስገዳጅ ሥምምነት እንዲኖር ትፈልጋለች የሚሉት ፕሮፌሰር ኢስላም የግብጽ አካሄድ ሦስቱ ሀገራት የተፈራረሙበትን የ2015 ስምምነት የሚጥስ ከመኾኑም በላይ የዓለም አቀፍ የውኃ ስምምነትን የሚጻረር ነው ብለዋል፡፡ ዓለም አቀፍ የውኃ ሥምምነቶች አስገዳጅነት የሌላቸው እና በዋነኛነት በመልካም ፈቃድ ላይ የተመሰረቱ በመኾናቸው አስገዳጅ ሥምምነቶችን ተግባራዊ ማድረግ ፈታኝ እንደኾነ ያነሳሉ፡፡

ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ የምትገነባው ግድብ በግዛቷ ውስጥ ያለን ጸጋ አልምቶ የመጠቀም ሉዓላዊ መብት ተደርጎ ይወሰዳል የሚሉት የውኃ ተመራማሪው ዓለም አቀፍ ሕጎች ይህንን መብት የሚጻረሩበት መብትም ኾነ የሕግ ክፍተት የላቸውም ነው የሚሉት፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ወሰን ተሻጋሪ የውኃ ስምምነትን ጨምሮ ሌሎች ዓለም አቀፍ ሕጎች አንዱ ሀገር ሌላውን ሀገር ፈጽሞ በማይጎዳበት መንገድ መጠቀምን ይደነግጋሉ፡፡ ኢትዮጵያም ኾነች ግብጽ አስገዳጅ ስምምነቶችን የሚፈርሙበት ግዴታ የለም ይላሉ ፕሮፌሰር ሻፊቁል ኢስላም፡፡

ኢትዮጵያ ግድቡን የምትገነባው የትኛውንም ሀገር ለመጉዳት ሳይኾን ከግማሽ በላይ ዜጎቿ በጨለማ ውስጥ የሚኖሩ በመኾናቸው የኤሌክትሪክ ኀይል ተጠቃሚ ለማድረግ ነው የሚሉት የውኃ ተመራማሪው ይህ ደግሞ የመልማት ብቻ ሳይኾን የሰብዓዊነትም ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡ የግድቡ ግንባታ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ ከ5 ሺህ 200 ሜጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኀይል የማመንጨት አቅም አለው፡፡ ይህም ሀገሪቱ የውስጥ ፍላጎቷን ከማሟላት ባለፈ ለጎረቤት ሀገራት ኤሌክትሪክ በመላክ ቀጣናዊ ትስስሩን ታጠናክራለች ነው ያሉት፡፡

ፕሮፌሰር ሻፊቁል ኢስላም ኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብታዊ እድገቷን ለማስቀጠል እና ራሷን ችላ ለመንቀሳቀስ ያላትን ቁርጠኝነት እንደሚያመላክት ገልጸው ከዓለም አቀፍ ደንቦች እና ከጎረቤት ሀገራት ጥቅም አንፃርም ቢኾን ቅቡል ነው ይላሉ፡፡
በአጠቃላይ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት በዓለም አቀፍ የውኃ አሥተዳደር ውስጥ ያለውን ውስብስብነት ያሳያል የሚሉት ፕሮፌሰር ሻፊቁል ኢስላም ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ንግግር፣ ትብብር እና ሁለንተናዊ የጋራ ተጠቃሚነትን ማስፈን ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያ ከትብብር አንጻር የያዘችው ጠንካራ አቋም ከሕግም ኾነ ከሞራል ያላፈነገጠ በሳል አካሄድ ነው ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የግብርናዉን ዘርፍ ለማዛመን አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች በፋይናንስ መደገፍ አለባቸዉ” የግብርና ሚኒስቴር
Next articleበክልሉ ስምንት ዞኖች የወባ የሕሙማን ቁጥር እየጨመረ እንደሚገኝ ተገለጸ፡፡