
ባሕር ዳር: ሰኔ 12/2015 ዓ.ም (አሚኮ) አማራ ክልል በርካታ የግንባታ ማዕድናት ባለቤት ነው። ላይምስቶን፣ ሳንድስቶን፣ እብነበረድ፣ ጥቁር ድንጋይ፣ ኖራ ድንጋይ፣ ካልሳይት፣ ቤንቶናይት፣ ሲሊካሳንድ እና የመሳሰሉት ማዕድናት በክልሉ በርካታ አካባቢዎች በስፋት እንደሚገኙ የዘርፉ ባለሙያዎች ይጠቁማሉ። እንደ ወርቅ፣ ኦፓል፣ ብረት፣ ኤመራልድ እና የመሳሰሉ የከበሩ ማዕድናትም የአማራ ክልል ገጸ በረከቶች ናቸው።
ቀደም ሲል እስከ ዞን፣ ወረዳ እና ቀበሌ ዘልቆ የማዕድን ዘርፉን የሚመራ ራሱን የቻለ መዋቅር አልነበረም። ይህም በየቦታው የሚገኙ ማዕድናት ባለቤት አልባ ኾነው በሕገ ወጦች ብቻ ተይዘው እንዲቸበቸቡ ምቹ ሁኔታን ፈጥሮ ቆይቷል።
አሁን ላይ ከፌደራል እስከ ቀበሌ ድረስ የማዕድን ዘርፉን የሚመራ መዋቅር ተዘርግቷል። በማዕድናት ተጠቃሚ ለመኾን “ማዕድን አዲሱ የንጋት ተስፋ ለክልላችን” በሚል መሪ ሃሳብ የአማራ ክልል ማዕድን ሃብት ልማት ቢሮ በተዋረድ እየሠራ ይገኛል።
ለወጣቶች የሥራ እድል ለመፍጠር፣ የክልሉን እና የሀገርን ምጣኔ ሃብትም ለመደገፍ ከሚያገለግሉ ማዕድናት ውስጥ ኦፓል አንዱ ነው። ይህ ማዕድን በክልሉ የተለያዩ ቦታዎች የሚገኝ ሲኾን በሰሜን ወሎ ዞን ጋዞ እና ደላንታ ወረዳዎች በስፋት አለ። ኦፓል ለአካባቢው በጸጋነት የተሰጠ ቢኾንም ከሕገ ወጦች ጸድቶ ተገቢውን ጥቅም እየሰጠ አለመኾኑን የጋዞ ወረዳ ማዕድን ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ቢክስ ተስፋው አንስተዋል። ቀደም ሲል ኦፓል የማምረት ተግባር በሕገ ወጦች ብቻ ተይዞ የቆየ እንደነበር ነው የተናገሩት። እነዚህ አካላት ከየት እንደመጡ፣ እንዴት እንደሚያመርቱ እና እንደሚሸጡ አይታወቅም ነበር ብለዋል ኅላፊው። ወረዳውም የማስቆም አቅም የለውም ነበር ሲሉም ተናግረዋል።
አሁን ላይ ወጣቶች እየተደራጁ እንዲያመርቱ እና ትክክለኛ የግብይት መንገዶችን ተጠቅመው ሃብት እንዲያመነጩ እየተሠራ ስለመኾኑም አንስተዋል። ከ25 በላይ ማኅበራት ተቋቁመው ፈቃድ በመውሰድ በማምረት ላይ እንደሚገኙም ገልጸዋል። ምርቱ ሰንሰለቱን በጠበቀ መልኩ ለገበያ ሲቀርብ ለአካባቢው ብሎም ለሀገር ገቢ ያስገኛል ነው ያሉት።
አቶ ቢክስ በኦፓል ምርት ላይ ተንሰራፍቶ የቆየው ሕገ ወጥነት ቀነሰ እንጅ ጨርሶ አለመጽዳቱን ተናግረዋል። አሁንም ድረስ በሕገ ወጥ መንገድ የሚያመርቱ እና የሕጋዊ አምራቾችን ጥቅም የሚያሳጡ አካላት መኖራቸውን ጠቁመዋል። ምርቱን የሚሸጡበት መንገድም ትክክለኛውን የግብይት ሰንሰለት ያልተከተለ በመኾኑ የሀገርን ጥቅም የሚጎዳ ነው ብለዋል። “ሕገ ወጦች እጃቸው ረጅም ነው” ያሉት አቶ ቢክስ በወረዳው አቅም ብቻ መከላከል ስለማይቻል የሚመለከተው ሁሉም ተረባርቦ የማዕድን ዘርፉን ከሕገ ወጥነት ማጽዳት ያስፈልጋል ብለዋል።
የአማራ ክልል ማዕድን ሃብት ልማት ቢሮ ኀላፊ ሀይሌ አበበ በበኩላቸው “ሕገ ወጥነት የማዕድን ዘርፉ አንዱ ማነቆ ነው” ብለዋል። ከአሸዋ እና ጠጠር ጀምሮ የከበሩ ማዕድናትን ጭምር በሕገ ወጥነት ለመጠቀም የሚሞክሩ አካላት በርካታ ናቸው ነው ያሉት። በተለይም የኦፓል ምርት በሕገ ወጥ ደላላዎች እጅ እየወደቀ በኮንትሮባንድ መልኩ ወደ ውጭ እንዲወጣ እየተደረገ ነው ብለዋል። በየአካባቢው የሚያመርቱ ወጣቶች በልፋታቸው ልክ ሳይጠቀሙ፤ ሀገርም የሚገባትን ገቢ ሳታገኝ ለሕገ ወጦች መክበሪያ እየኾነም ቆይቷል ነው ያሉት።
በማዕድን ዘርፍ የሚታየውን ሕገ ወጥነት ለመቆጣጠር በማዕድን ሚኒስቴር እና ፌዴራል ፓሊስ ኮሚሽን የጋራ ውይይቶች ተደርገዋል ነው ያሉት። በዞን እና ወረዳዎች የተዘረጋው የማዕድን አደረጃጀት አሠራር አበጅቶ ሕገ ወጥነትን መታገል እንደሚገባም ተናግረዋል።
የማዕድን ሃብት ቁጥጥር ግብረ ኀይል መቋቋሙንም አቶ ሀይሌ ተናግረዋል። ግብረ ኀይሉ ከርዕሰ መሥተዳድር ጀምሮ በየደረጃው የሚገኙ የሥራ ኀላፊዎችን ያካተተ ነው። ይህ ግብረ ኀይል የማዕድን ሥራ ሕጋዊነትን በተላበሰ መልኩ እንዲከናወን እና ዘርፉ ተገቢውን ጥቅም እንዲሰጥ ማስቻል እንዳለበትም መልዕክት አስተላልፈዋል።
የክልሉ ማዕድን ሃብት ልማት ቢሮ ከጸጥታ አካላት እና ከገቢዎች ቢሮ ጋር ቅንጅታዊ አሠራር ፈጥሮ በማዕድን ዘርፉ ሕጋዊ አሠራርን ለማስፈን እየተንቀሳቀሰ ስለመኾኑም አቶ ኀይሌ ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦ አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!