ደም በመለገስ በደም መፍሰስ ምክንያት ሊያልፍ የሚችለውን የሰው ሕይወት መታደግ እንደሚገባ ተጠየቀ።

105

ባሕር ዳር: ሰኔ 11/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ደም ባንክ በ2015 ዓ.ም ደም በመለገስና በማሰባሰብ ለተሳተፉ ተቋማት፣ ክበባትና ግለሰቦች የምሥጋና መርሐ ግብር አዘጋጅቷል። በተከታታይ ደም ከለገሱት በጎ ፈቃደኞች ውስጥ ዲያቆን ይርጋለም አሻግሬ አንዱ ነው። በባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ጤና መምሪያ ባለሙያ የኾነው ዲያቆን ይርጋለም አሻግሬ ከ32 ጊዜ በላይ ደም እንደለገሰ ነው የነገረን። ደም በተፈጥሮ ኡደት እንደሚወገድ የገለጸው ባለሙያው በተፈጥሮ የሚወገድን ደም በመለገስ በደም መፍሰስ የሚያልፍን ሕይወት መታደግ እንደሚገባ መክሯል። በቀጣይም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው ያነሳው። ሌላኛዋ ደም ለጋሽ ፍሬሕይወት ሙስጦፋም 32 ጊዜ ደም ለግሳለች። ደም ለጋሿ እንዳለችው ደም በመለገስ በደም መፍሰስ ሊያልፍ የሚችለውን የሰው ሕይወት መታደግ ሰው ኾኖ ለተፈጠረ ሁሉ መርሕ ሊኾን ይገባል።

የባሕርዳር ደም ባንክ ኀላፊ ምክሩ ሽፈራው እንደገለጹት የባሕርዳር ደም ባንክ በ2015 ዓ.ም ለመሰብሰብ 22 ሺህ ከረጢት ደም አቅዶ፣ ከ25 ሺህ በላይ ከረጢት በመሰብሰብ ለጤና ተቋማት አሰራጭቷል። የደም ባንኩ ከደም ለጋሽ ክበቦች፣ ከትምህርት ቤቶች እና ከማኅበረሰቡ መሠብሰቡን ነው የገለጹት። አልፎ አልፎ በክረምትና ትምሕርት ቤቶች በሚዘጉበት ወቅት ከሚያጋጥም የደም አይነት መቆራረጥ ውጭ የደም እጥረት አለማጋጠሙንም አንስተዋል። ደም ባንኩ በባሕርዳር ከተማ ለሚገኙ 34 ሆስፒታሎች ነው ደም የሚያቀርበው ። በክረምት ወራትም ከበጎ ፈቃደኞች እና ከማኅበረሰቡ ደም ለመሰብሰብ ማቀዳቸውን ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኀላፊ አብዱልከሪም መንግሥቱ እንዳሉት በድንገተኛ የመኪና አደጋ እና በወሊድ ጊዜ የሚያጋጥምን የደም መፍሰስ ለመከላከል ደም የማሰባሰብ ሥራ ሲሠራ ቆይቷል። በበጀት ዓመቱ በክልሉ በሚገኙ አስር ደም ባንኮች ከ78 ሺህ በላይ ዩኒት ደም መሰብሰቡን ገልጸዋል። ይህም ለመሰብሰብ ከተቀመጠው እቅድ 90 በመቶ በላይ ተከናውኗል ነው ያሉት።ቢሮው ቋሚ የደም ለጋሾችን ለማፍራት እየሠራ መኾኑንም አንስተዋል። ማንኛውም ሰው ደም በመለገስ በደም መፍሰስ ምክንያት ሊያልፍ የሚችለውን የሰው ሕይወት የመታደግ ኀላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል። የባሕር ዳር ደም ባንክ ለተከታታይ 4 ዓመታት በኢትዮጵያ ከሚገኙ 43 የደም ባንኮች በቀዳሚነት መቀመጡ ተነስቷል።

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የአማራ ማንነታችን በአፋጣኝ ሕጋዊ ዕውቅና ይሰጠን” የምሥራቅ ጠለምት ወረዳ ነዋሪዎች
Next articleበኩር ጋዜጣ ሰኔ 12/2015 ዓ.ም