
ባሕር ዳር: ሰኔ 11/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በውስጡ እልፍ ሕይዎት ያላቸው አዕዋፍት እና ፍጥረታት የከተሙበት ሐይቅ ቢኾንም ዝምታው ግን ፈጽሞ ያስፈራል፡፡ ጸጥታው ሰብዓዊ ፍጡራንን ያቀፈ እና ዘረ ብዙ እጽዋትን የታቀፈ የሐይቆች ንጉሥ ስለመኾኑ ይመሰክራል፡፡ ቅዱስ የኾነው ሐይቅ ዓለማዊ እና መንፈሳዊ ሕይዎት ሳይጋጩ የሚመሩበት የሠላም ተምሳሌት ነው፡፡
እርጋታው ዘጠኝ ሜትር የሚርቅ የውኃ ጋን ሳይኾን በጽኑ መሠረት ተፈጥሮ ያጸናችው የዓለት ሥር ወለል ይመስላል፡፡ አድማስ የማይወስነውን እና የተንጣለለውን የጣና ሐይቅ አጽናፍ አስተውሎ ላየው ውኃ ሳይኾን የሰማይ ስባሪ ይመስላል፡፡
የሀገራቸውን ጥንታዊ እና ታሪካዊ ሰንደቅ ዓላማ እያውለበለቡ በሐይቁ ላይ የሚከንፉት ትናንሽ ጀልባዎች የሠላም መልዕክተኛ ይመስላሉ፡፡ በሐይቁ ዳርቻ አካባቢ ልብሳቸውን የሚያጥቡ እና የሚታጠቡ የሀገሬው ሰዎች የጣናን ሐይቅ ምስጢራዊነት የተላመዱ ቤተኞች ናቸው፡፡ የገዳማት በረከት የበዛለት እና የደሴቶች ጉርብትና ብርቅ ያልኾነበት የጣና ሐይቅ ሰማያዊው የውኃ ቀለም እስከ ሰማየ ሰማያት የደረሰ የሃሴት ምንጭ ነው፡፡ የአህጉሪቷ አነጋጋሪ ታላቅ ወንዝ የኾነው የዓባይ ወንዝ ገና ከመነሻው በጣና ሐይቅ ላይ አቋርጦ ሲሄድ መመልከት እስከ ሜድትራኒያን ለማሰብ እና ለማንሰላሰል ያስገድዳል፡፡
ከውቢቷ ባሕር ዳር እስከ ታሪካዊቷ ጎንደር፤ ከለምለሙ የጎጃም ምድር እስከ ማማው በጌምድር የሚዘረጋው የጣና ሐይቅ ስፋት የታላቋ ኢትዮጵያ ተምሳሌት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ በደቡብ የቤዛዊት ቤተ መንግሥት እና በሰሜን የጎንደር አብያተ መንግሥታት ለክብሩ ዘብ ቆመዋል፡፡ በምዕራብ የጉዛራ እና በምሥራቅ የሱስንየስ አብያተ መንግሥታት ተጋርደውለታል፡፡
ታሪክ፣ ባሕል፣ ሃይማኖት፣ ማንነት እና ማራኪ መልካ ምድር በአንድ ተጠቃለው በዚህ ሐይቅ ውስጥ ተንሰላስለው ይታያሉ፡፡ በጥንታዊ ሥልጣኔ እና በሀገር በቀል ዕውቀት ከቀደምት የዓለም ሀገራት ተርታ የምትሰለፈው ኢትዮጵያ መረጃዋም ማስረጃዋም ጣና ሐይቅ ላይ ሰጥሟል፡፡ በዚህ ሐይቅ ውስጥ ከሰው ዘር መገኛዋ ሀገር አቢሲኒያ እስከ ነጻዋ ሀገር ኢትዮጵያ ድረስ ያልተቋረጠ ታሪክ ድርና ማግ ኾኖ ተንሰላስሏል፡፡
ከገሊላ ዘካሪያስ እስከ ገዳመ እንጦስ፣ ከዋሻ እንድሪያስ እስከ ዳጋ እስጢፋኖስ፣ ከቢርጊዳ ማርያም እስከ ሬማ መድሐኒ ዓለም፣ ከኡራ ኪዳነ ምሕረት እስከ አርሴማ ሰማዕት፣ ከደብረ ሲና ማርያም እስከ ደብረ ማርያም የዘመንን ረጂም ጎዳና ከትብው ያሳለፉ የዕውቀት፣ የማንነት እና የመቼነትን መልስ የያዙ የጣና ሐይቅ ውስጥ ምስክሮች እነዚህ ብቻ አይደሉም፡፡
ጣና ከሐይቅነቱ ይልቅ ምስጢራዊነቱ ይልቃል፡፡ ያልተረዳነው እውነት፣ ያልተገነዘብነው ዕውቀት፣ ያልተቀበልነው ማንነት፣ ያልተላበስነው እሴት፣ ያልኖርነው አብሮነት እና ያላከበርነው ታላቅነት በዚህ ሐይቅ ውስጥ በአርምሞ ይታዘበናል፡፡
ኢትዮጵያ ለመሪዎቿ የሚበጅ የመሪነት ጥበብ እና ለተተኪዎቿ የሚስማማ መማሪያ ክበብ በጣና ሐይቅ ገዳማት ውስጥ የከተሙ ዘመን ተሻጋሪ ድርሳናት ቢኖሯትም አገላብጦ ያያቸው የለም፡፡ ኢትዮጵያውያን የጠበበቻቸው መስሏቸው በሚጋፉባት የኢትዮጵያ ሰማይ ስር አድማስ በማይወስነው ሰፊ ሐይቅ ውስጥ ለሁሉም የሚበቃ ፍቅር እና መከባበር ስለመኖሩ ለአፍታ እንኳን አላሰቡትም፡፡ የጣና ሐይቅ ምስጢራዊነት ለኢትዮጵያዊያን ተገልጦ እና አሁን ያለው ታሪካቸው ተገልብጦ እስኪታይ ድረስ ኢትዮጵያዊነትን ጠብቆ እና ማስረጃዎቿን አርቆ ያቆየውን ሐይቅ መጠበቅ ግን የውዴታ ግዴታ ነው፡፡
የጣና ሐይቅ፣ በውስጡ ያሉት ገዳማት እና በዙሪያው የከተሙት ተፈጥሯዊ መልካዓ ምድር የዓለም ቱሪስቶችን ቀልብ የመሳብ መግነ ጢሳዊ ኀይል የታደሉ ናቸው የሚሉት በኢትዮጵያ ቅርስ ጥናት እና ጥበቃ ባለሥልጣን የዓለም አቀፍ ቅርስ ሰነድ ዝግጅት ከፍተኛ ባለሙያ ተስፋ አራጌ ናቸው፡፡ የጣና ሐይቅ ተፈጥሯዊ ጸጋዎችን ለዓለም ሕዝብ አስተዋውቆ ጎብኝዎች እንዲመላለሱባቸው ለማድረግ ብዙ ጥረት የሚጠይቅ አልነበረም የሚሉት ባለሙያው ጉዳዩን በትኩረት ይዞ አለመሥራት ለሐይቁ የህልውና ስጋት እና በጎብኝዎች አዕምሮ ውስጥ ለመረሳት ዳርጎታል ይላሉ፡፡
በቅርቡ የክልሉ መንግሥት ቅርሱ በዓለም የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) እንዲመዘገብለት ጥያቄ አቅርቦ እንደነበር ያነሱት ከፍተኛ ባለሙያው ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ጥያቄውን ተቀብሎ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ሲሠራ እንደቆየ ነግረውናል፡፡ ላለፉት ሁለት ዓመታት የአዋጭነት ጥናት ተዘጋጅቶ የጥናት ውጤቱ የጣና ሐይቅ ደሴተ ገዳማት እና አዋሳኝ ባሕር ሸሽ አካባቢዎች መልካዓ ምድር ባሕላዊ እና ተፈጥሯዊ ቅርስ የዓለም ቅርስ መዝገብ ውስጥ ቢካተት አዋጭ እንደሚኾን ያመላክታል፡፡ ከጥናት ውጤቱ በኋላም የቅርስ መምረጫ እና አሥተዳደር ሰነዶች ዝግጅት ተጀምሯል ነው ያሉን ባለሙያው፡፡
የጣና ሐይቅ ደሴተ ገደማት እና አዋሳኝ ባሕር ሸሽ መልካ ምድር በዩኔስኮ መመዝገባቸው ሁለት መሠረታዊ ጥቅሞች አሉት ያሉት ከፍተኛ ባለሙያው በርካታ ሰው ሠራሽ አደጋዎች ለተደቀኑበት የሐይቁ ከባቢ ዋስትና ለመስጠት ምዝገባው ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡ በሌላ በኩል ቱሪስቶች አንድን አካባቢ ለመጎብኘት መጀመሪያ የሚመለከቱት በዩኔስኮ የተመዘገበ ቅርስ በመኾኑ የመረጃ ምንጭ ኾኖ ያገለግላል፡፡ በተጨማሪም የጣና ሐይቅ አካባቢ በዩኔስኮ መመዝገባቸው ብሔራዊ ኩራት፣ የማንነት መገለጫ እና ለቀጣዩ ትውልድ ተጠብቆ የሚተላለፍ ኾናል ብለዋል፡፡
የጣና ሐይቅ ጸጋዎችን እንኳን የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ኢትዮጵያዊያን እንኳን በወጉ አናውቀውም የሚሉት ከፍተኛ ባለሙያው በቀጣይ ሐይቁን እና የሐይቁን ጸጋዎች በተገቢው ልክ ማስተዋወቅ የቤት ሥራ ነው ብለዋል፡፡ ምስጢራዊው ሐይቅ ምስጢራዊቷን ሀገር ይጠብቃል፤ እስከዚያው ግን ምስጢራዊውን ሐይቅ መጠበቅ እና መንከባከብ የትውልድ፣ የመንግሥት እና የሕዝብ የውዴታ ግዴታ ነው፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!