“የአማራ ማንነታችን በአፋጣኝ ሕጋዊ ዕውቅና ይሰጠን” የምሥራቅ ጠለምት ወረዳ ነዋሪዎች

310

ባሕር ዳር: ሰኔ 11/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ምሥራቅ ጠለምት ወረዳ ልክ እንደ ወልቃይትና ራያ ኹሉ ለሦስት አስርት ዓመታት ከማንነቱ ውጪ በህወሃት በኀይል ተወስዶ በቋንቋው እንዳይናገር፤ ባሕሉን እንዳያሳድግ፤ በሀብቱ ልክ እንዳይለማ አፈና ሲፈጸምበት ቆይቷል። አካባቢው ባለፉት 30 ዓመታት በልጆቹ ቆራጥ ተጋድሎና ከፍተኛ መስዋእትነት ከአፋኝ ኀይሉ ነጻ መውጣት ችሏል።

በዛሬው እለትም ነጻ የወጡት የምሥራቅ ጠለምት ወረዳ ነዋሪዎች ሰላማዊ ሰልፍ እያደረጉ ይገኛሉ። ነዋሪዎቹ በሰላማዊ ሰልፋቸው ለፌዴራል መንግሥትና ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የተለያዩ ጥያቄዎችና መልእክቶችን አቅርበዋል።

በሰላማዊ ሰልፉ፦

👉እኛ የምሥራቅ ጠለምት ወረዳ ነዋሪዎች አማራ ነን እንጅ አማራ እንሁን አላልንም።ሥለኾነም የፌዴራል መንግሥት ለአማራነት ማንነታችን አፋጣኝ ሕጋዊ ዕውቅና ይሰጠን ዘንድ እንጠይቃለን ነው ያሉት።

👉ምሥራቅ ጠለምት ወረዳ ለረጅም ጊዜ ጦርነት የነበረበትና በርካታ ውድመት ያስተናገደ በመኾኑ አርሶ አደሩ ከልማት ርቆ ስለቆየ መንግሥት የወደሙ ተቋማትን መልሶ እንዲያቋቁምና የሰብአዊ እርዳታም እንዲያደርሰን እንጠይቃለን ብለዋል።

👉 የፌዴራል መንግሥት በወረዳው ለሚገኙ የመንግሥት ተቋማት ጤና ጣቢያዎች፣ ትምህርት ቤቶችና ሌሎች አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ከሥራ ውጭ በመኾናቸው ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል። ስለኾነም መንግሥት ለወረዳው መፍትሔ ሊሰጥ ይገባል ብለዋል ሰልፈኞቹ።

በሰልፉ የምሥራቅ ጠለምት ወረዳ ነዋሪዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የዞንና የወረዳ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎችና ሠራተኞች፣ በውጭ የሚኖሩ የጠለምት ተወላጅ ማኅበራት አባላት፣ የከፋኝ ታጋይ ቤተሰቦችና ሌሎችም ተሳትፈዋል።

ዘጋቢ፦አድኖ ማርቆስ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ጥቅሙን አውቀነዋልና ችግኝ መትከል አናቆምም” የባንጃ ወረዳ አርሶ አደር
Next articleምስጢራዊው ሐይቅ፡ ጣና