
ባሕር ዳር: ሰኔ 11/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በሩቅ ለሚያያት አረንጓዴ ካባ የደረበች ሙሽራ ትመስላለች፡፡ አልፎ አልፎ ከሚታዩ የእርሻ ማሳዎች ውጭ ነፃ ኾኖ የሚታይ መሬት የለም፡፡ እየቀረቡ ሲሄዱ ለመቁጠር የሚያስቸግር ዲከረንስ የተባለ ዛፍ በስፋት ይታያል፡፡ አዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ባንጃ ወረዳ ኣሰም ስላሴ ቀበሌ ተገኝተናል፡፡
ለልማት የወጡት አርሶ አደሮች ሥራቸውን ከሚያቀላጥፉበት ቦታ ስንደርስ አርሶ አደሮቹ የወል የመሬታቸውን በችግኝ ለመሸፈን የወሰኑትን ውሳኔ ምድር ላይ ለማውረድ የቀደማቸው የለም፣ በሕብረት ይተክላሉ፡፡
አርሶ አደር አለቃ ሰማ ከእነዚህ አርሶ አደሮች ውስጥ አንዱ ናቸው፡፡ አርሶአደር አለቃ የመቀስቀሻውን ጡሩንባ ደጋግመው ያስጮሁታል። የአካባቢው አርሶ አደር ከቤቱ ያለውን መቆፈሪያ እየያዘ ልማት ቦታው ላይ ተገኝቷል። በችግኝ ተከላ ልማቱ ወጣቶች፣ ሴቶች እና አዛውንቶች እየተሳተፉ ነው።
በአካባቢው የዲከረንስ ችግኝ በብዛት ለከሰል ይፈለጋል። ችግኙ በሁለት ዓመት ውስጥ መሬቱን ወደ ነበረበት ለምነት ቀይሮ የተሻለ ምርት እንዲገኝም ጠቀሜታው የጎላ ነው። ይህ ዛፍ የነበረበት መሬት በአጭር ጊዜ ለም ስለሚኾን ማኛ ጤፍ እና ገብስ ይዘራበታል። ለዚህም ነው አርሶ አደሮቹ ማሳቸውን እያቀያየሩ ይህን ዛፍ ለመትከል እና ለማጽደቅ የሚሽቀዳደሙት።
መጣሁ መጣሁ የሚለውን ዝናብ ያዘለ ደመና ለመቅደም ሁሉም በያዘው መሣሪያ ጉድጓድ ይቆፍራል። ቦታው ተራራማ በመኾኑ አፈሩን ለማስቀረት ጉድጓዱን አዝልቀው ይቆፍሩታል።
በየዓመቱ በጋራ ከሚያለሙት የወል መሬት ችግኝ በጋራ ሽጠው እንደሚጠቀሙ አርሶ አደር አለቃ ሰማ ነግረውናል። አርሶ አደር አለቃ በጋራ ከሚተከሉ የወል ማሳዎች በተጨማሪ በግል ማሳቸው የመትከል ልምዳቸው ሰፋ ያለ መኾኑን አጫወቱን፡፡ ባለፉት ዓመታት የተተከለው የዲከረንስ ችግኝ ለሽያጭ ደርሶ ተጠቃሚ አድርጓቸዋል፡፡ ቤት ሠርተዋል፣ ለልጃቸው ባጃጅ ገዝተው ሰጥተዋል፣ ቀሪዎችን ልጆችም እያስተማሩ ነው፡፡ ካሳለፋት የችግር ዘመን ያወጣቸው የተተከለው ችግኝ ተሸጦ ነው፡፡ በተከሉት ችግኝ መሬታቸው አገግሟል፡፡ በየሁለት ዓመቱ የሚቀያየረው መሬት ምርታማነቱ ጨምሯል፡፡ ዛሬ ለእሳቸው ድኅነት ታሪክ ኾኗል፡፡ በልማት በሚተከለው የዲከረንስ ችግኝም የድርሻቸውን ሊወጡ ደፋ ቀና ይላሉ፡፡ መሬት ጦም ማደር የለበትም ባዩ ጀግና ገበሬ ከእሳቸው ማሳ አልፎ የሌሎችንም ተከራይተው በመትከል ውጤት አምጥተዋል። “ጥቅሙን አውቀነዋልና ችግኝ መትከል አናቆምም” ብለዋል።
በችግኙ ሥር በሚበቅል ሳር ደግሞ በሬዎቻቸውን ያደልባሉ፡፡ “ጥሩ ገቢ እያገኘሁ ነው፡፡ ችግኝ መትከል አላቆምም” ብለዋል፡፡ ችግኙ ለሌሎች ወጣቶች የሥራ እድል እየፈጠረ በመኾኑ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት የሚለው ሃሳባቸው ደግሞ ከሌሎች ሃሳቦች ጎልቶ ይሰማል፡፡
በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር በባንጃ ወረዳ የኣሰም ስላሴ ችግኝ ጣቢያ ኀላፊ ጌታቸው አበበ የአርሶ አደሮችን ሕይወት የሚቀይሩ ከ200 ሺህ በላይ ችግኞች ተዘጋጅተዋል ብለውናል፡፡ የተሠጣቸውን ኀላፊነት በአግባቡ ለመወጣት ጠንክርው በመሥራታቸው ችግኞቹ ከመጠን በላይ ማደጋቸውን እና ለሥርጭት ዝግጅት መደረጉን አንስተዋል፡፡ ለአርሶ አደሮች ሙያዊ ድጋፍ በማድረጋቸውም ከሚተከሉ ችግኞች የሚደርቅ የለም ነው ያሉት፡፡ ግራቢሊያ፣ ዲከረንስ፣ እና የሃበሻ ጽድ በኣሰም ችግኝ ጣቢያ ከተዘጋጁ ችግኞች ዋና ዋናዎቹ ናቸው ብለዋል፡፡
በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር የባንጃ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ወርቅነህ ዳኛው በዞኑ የደን ልማት ቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተሠሩ መኾኑን አንስተዋል፡፡ በዚህም 1 ሺህ 200 ሄክታር መሬት ለተካላ መዘጋጀቱንም ጠቁመዋል፡፡ ከ11 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ችግኝ ለተከላ የተዘጋጀ ሲኾን 11 ሚሊዮን ችግኞች ለተከላ ዝግጁ መኾናቸው ተረጋግጧል ነው ያሉት፡፡
አቶ ወርቅነህ በዞኑ የአንድ ቀን የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር የሚተከሉ 4 ነጥብ 3 ሚሊዮን ችግኞች ተለይተው መዘጋጀታቸውንም ጠቁመዋል፡፡ ችግኞቹ በ432 ሄክታር መሬት ላይ እንደሚተከሉም ነው የተናገሩት። የተዘጋጁ ችግኞች በብዛት በግለሰብ ማሣ ላይ የሚተከሉ ይሁኑ እንጅ በወል መሬት በተቋማት እና በተሠሩ ተፋሰሶች የሚተከሉ ናቸው፡፡ አርሶ አደሮች በተደጋጋሚ በተከሉት ችግኝ ከማምረት የወጡ ማሳዎች ወደ ማምረት መመለሳቸውንም አቶ ወርቅነህ አስገንዝበዋል፡፡
የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ ኀላፊ ታደሰ አስፋው(ዶ.ር) በዞኑ ከ77 ነጥብ5 ሚሊዮን በላይ ችግኝ ለተከላ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።ችግኞቹ የሚተከሉበት ከ950 ሄክታር በላይ መሬት ተለይቶ እስከ 50 መሊዮን የሚደርሱ ጉድጓዶች መቆፈራቸውን ነው ያነሱት።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃ እና አጠቃቀም ዳይሬክተር እስመለዓለም ምህርት በክልሉ ከ1 ነጥብ 55 ቢሊዮን በላይ ችግኝ ለተከላ መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡ እስካሁን 1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ጉድጓዶች ተቆፍረዋል፡፡ ችግኙ በደን በጥምር ደን እርሻ እና በበጋ በተሠሩ ሥነ አካላዊ ሥራዎች ላይ የሚተከሉ መኾናቸውን ዳይሬክተሩ አንስተዋል፡፡ በተከላ ወቅትም ከ307 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ለማሳተፍ መታቀዱን ጠቁመዋል፡፡
ዘጋቢ ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!