
ባሕር ዳር፡ ሕዳር 21/2012ዓ.ም (አብመድ) በስፌት ሥራ የሚተዳደሩ ሴቶች ለስፌት አገልግሎት ግብዓት የሚውለው የደንገል ተክል እየተመናመነ በመምጣቱ መቸገራቸውን አስታወቁ፡፡
በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር በባሕላዊ የሞሰብ፣ አገልግል፣ ሰፌድ፣ የሾፌሮች መቀመጫ እና የእንጀራ መሳቢያ በመስፋት ለገበያ እያቀረቡ የሚተዳደሩ ሴቶች በርካታ ናቸው፡፡ አሁን አሁን ግን ለጥሬ እቃነት የሚያገለግለው የደንገል ተክል እየቀነሰ በመምጣቱ ስፌት ሰፍቶ ለገበያ ለማቅረብ እየተቸገሩ እንደሆነ በደንገል ስፌት የሚተዳደሩት የ75 ዓመቷ አዛውንት ወይዘሮ ደመቁ ሰማኝ ተናግረዋል፡፡
ደንገል የሚበቅልበት የጣና አካባቢ የተፈጥሮ ሀብት መመናመን፣ የደንገል ራስ ለጨፌነት በስፋት ስለሚውል በየጊዜውና በብዛት መቆረጡና መነቀሉ እንዲሁም ሌሎች እርሳቸው የማያውቋቸው ምክንያቶች ተደማምረው የደንገል ተክል እየቀነሰ መመጣቱን፤ በዚህም መቸገራቸውን ገልጸዋል፡፡
‹‹ቀደም ሲል 3ዐ ብር ይሸጥ የነበረ የእንጀራ ሞሶብ ዛሬ እስከ 5ዐዐ ብር ደርሷል›› ያሉት ወይዘሮ ደመቁ ሁኔታው አሳሳቢ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ከልጅነታቸው ጀምሮ በዚሁ ሥራ ዕሜያቸውን ሙሉ እንዳሳለፉ የሚናገሩት ወይዘሮ ደመቁ የመሸጫ ቦታ ቢሰጣቸውም የምርቱ ማከማቻና ማሳደሪያ ቦታ ግን ፈተና እንደሆነባቸውም ነው የገለጹት፡፡
የደንገል በጣና ሐይቅ ያለበትን ሁኔታ በተመለከተ የጠየቅናቸው የጣና ሐይቅና ሌሎች ውኃማ አካላት ጥበቃና ልማት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አያሌው ወንዴ (ዶክተር) እንዳሉት ጣና ዙሪያውን ከብቦት የነበረው ደንገል በውኃ ሸሽ እርሻዎችና በሌሎች ምክንያቶች ተራቁቶ በሐይቁ ደቡባዊ ዳርቻ ላይ ብቻ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ የደንገልን ኅልውና ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ እንደሆነም ዶክተር አያሌው አስታውቀዋል፡፡
በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ መምህርና የደንገል ኘሮጀክት ሐሳብ አመንጭና አስተባባሪ ንብረት አስራደ (ዶክተር) ደግሞ ‹‹የደንገልን ኅልውና ወደነበረበት ለመመለስ በባሕር ዳር ከተማ በተለያዩ ቦታዎች የማስፋፊያ ሥራ እየተሠራ ነው›› ብለዋል፡፡
በደንገል ስፌት ከሚተዳደሩ ሴቶች ከምርት ማከማቻና ማሳደሪያ ቦታ ጋር በተያያዘ ያለውን ችግር በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡት የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ምክትል ሥራ አስኪያጅ አንማው መኮንን ደግሞ በደንገል ስፌት ለሚተዳደሩ ሴቶች ከተደራጁ የመሥሪያ ቦታ ለመስጠት ከተማ አስተዳደሩ ዝግጁ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ እየሠሩ ያሉበት አካባቢ የእግረኛ መንገድ በመሆኑ ምቹ እንዳልሆነም ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ዘመንሽ አዱኛው