
ደሴ: ሰኔ 11/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት ከኢፌዴሪ የሕገ መንግሥትና ፌዴራሊዝም አስተምህሮ ማዕከል ጋር በመተባበር ከክልል ምክር ቤት ጀምሮ በየደረጃው ለሚገኙ አፈ-ጉባዔዎች በፌዴራሊዝም፣ በህብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝም እና የመንግሥታት ግንኙነት ላይ ግንዛቤ መፍጠርን ዓላማ ያደረገ የውይይት መድረክ በኮምቦልቻ ከተማ እየተካሄደ ነው።
በውይይት መድረኩ የሁሉም የአማራ ክልል ወረዳና ከተማ አሥተዳደር አፈጉ-ባዔዎች እየተሳተፉ ነው።
የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬ በመድረኩ ላይ ባስተላለፉት መልእክት “የሚገጥሙንን ሀገራዊና ክልላዊ ፈተናዎች ለመሻገር ኅብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝምን በተገቢው መንገድ መተግበር የፈተና መውጫው መንገድ ነው” ብለዋል።
የኢፌዴሪ የሕገመንግሥትና ፌዴራሊዝም አስተምህሮ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ኃይለኢየሱስ ታዬ (ዶ.ር ) ለአፈጉባዔዎች፣ በፌዴራሊዝም፣ ህብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝም እና የመንግሥታት ግንኙነት ላይ ግንዛቤ መፈጠሩ ማኅበረሰቡን በቀላሉ ተደራሽ ለማድረግ እንደሚያስችል ተናግረዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ ስልጠናው፣ አፈጉባዔዎች እንደየአካባቢያቸው ተጨባጭ ሁኔታ ባሕልና ወጋቸውን ጠብቀው በጋራ የኢትዮጵያን አንድነትና ሰላም ለማጠናከር ያግዛቸዋል ነው ያሉት።
በውይይት መድረኩ ከሁሉም የአማራ ክልል ወረዳና ከተማ አሥተዳደሮች የተውጣጡ ከ250 በላይ አፈጉ-ባዔዎች፣ የምክርቤት አመራር እና አባላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።
ዘጋቢ፦ ጀማል ይማም
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!