
ባሕር ዳር: ሰኔ 10/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን የጣና ሐይቅ ደሴተ ገዳማት እና አዋሳኝ ባሕር ሸሽ አካባቢን በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) ለማስመዝገብ የሚያስችል ዝግጅት እያደረገ መኾኑን አስታውቋል፡፡ በዩኔስኮ ጊዜያዊ መዝገብ ውስጥ የተካተተውን የጣና ሐይቅ ደሴተ ገዳማት እና አዋሳኝ ባሕር ሸሽ አካባቢን በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ ትብብር እና ቅልጥፍና ያስፈልጋል ተብሏል፡፡
ከ3 ሺህ 600 በላይ ኪሎ ሜትሮችን በሚያካልለው የጣና ሐይቅ ዙሪያ ታሪክ፣ ተፈጥሮ፣ ባሕል እና ሃይማኖታዊ ትውፊቶች ተንሰላስለው ከትመውበታል፡፡ ሚስጥራዊ ነው በሚባልለት በዚሁ ሐይቅ አካባቢ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጡ የሚማርክ፣ ተፈጥሯዊ ውበቱ መግነጢሳዊ የስበት ኅይል ያለው እና ተመርምሮ ያላለቀ እሴትና ማንነት እንዳለ ይነገራል፡፡ ጣና ውኃ ብቻ ሳይኾን የዓለምን ጎብኝዎች ስሜት የሚገዛ እና ቀልብ የሚያንጠለጥል ብዙ ጸጋዎችን በዙሪያው አቅፎ ይዟል፡፡ የዚህን ምስጢራዊ ሐይቅ ደሴት ገዳማት እና አዋሳኝ ባሕር ሸሽ አካባቢዎች በዓለም የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) ለማስመዝገብ የክልሉ መንግሥት ጥያቄ ካቀረበ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ምክትል ዳይሬክተር ኤሊያስ ሽኩር በዓለም ቅርስነት የይመዝገብልኝ ጥያቄው የቀረበው በክልሉ መንግሥት እንደኾነ ጠቅሰው በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እና በሌሎች ሂደቶች እስካሁን እንደቆየ አንስተዋል፡፡ የጣና ሐይቅ ደሴት ገደማት እና አዋሳኝ ባሕር ሸሽ አካባቢዎችን በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ የሚያስችል የአዋጭነት ጥናት ተካሂዷል ያሉት ምክትል ዳይሬክተሩ ከጥናቱ በኋላ በየደረጃው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቂ ውይይት እንደተደረገም ገልጸዋል፡፡
የጣና ሐይቅ አካባቢ በዩኔስኮ ጊዜያዊ ቅርስ መዝገብ ውስጥ ተካቷል ያሉት አቶ ኤሊያስ ዛሬ የተፈራረሙት የጣና ሐይቅ ደሴተ ገዳማት እና አዋሳኝ ባሕር ሸሽ መልክዓምድር፣ ባሕላዊ እና ተፈጥሯዊ ቅርስ የዓለም አቀፍ ቅርስ መምረጫ እና ቅርስ አሥተዳደር ሰነዶች ሥራ ፕሮጀክት የውል ሰምምነት ተፈራርመናል ብለዋል፡፡ የሰነድ ዝግጅቱን በመጪዎቹ 10 ወራት በማጠናቀቅ ለዩኔስኮ እንደሚላክም ምክትል ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ የሰነድ ዝግጅቱን በተያዘለት የጊዜ ገደብ ለማጠናቀቅ ትብብርና ፍጥነት ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡
የአማራ ክልል በርካታ ተፈጥሯዊ፣ ባሕላዊ፣ ታሪካዊ እና ሃይማኖታዊ ጸጋዎችን የታደለ ነው ያሉት የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ቢሮ ኅላፊ አየለ አናውጤ (ዶ.ር) ጸጋዎቹን አልምቶ በመጠቀም በኩል ገና ብዙ መሥራትን ይጠይቃል ነው ያሉት፡፡ እንደ ሀገር ኢትዮጵያ፤ እንደ ክልል አማራ በርካታ የዓለምን ጎብኝ ቀልብ የሚስቡ የቱሪስት መዳረሻዎች ቢኖሩትም በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡት ግን እጅግ ውስኖቹ ናቸው ብለዋል፡፡
የጣና ሐይቅ ደሴት ገዳማት እና አዋሳኝ ባሕር ሸሽ መልካ ምድር ባሕላዊ እና ተፈጥሯዊ ቅርሶች በዓለም ቅርስነት ከተመዘገቡ በስፋት ትልቁ በዩኔስኮ የተመዘገበ ቅርስ ይኾናል ያሉት ዶክተር አየለ ይህም የሐይቁን ደኅንነት ከማስጠበቅ ባሻገር የቱሪዝም እንቅስቃሴውን በማነቃቃት ድርሻው የጎላ ነው ብለዋል፡፡ ቱሪስቶች ለጉብኝት ከመንቀሳቀሳቸው በፊት በዓለም ቅርስነት የተመዘገበ የቱሪስ መዳረሻዎችን ቀድመው በተለያዩ አማራጮች ያያሉ ያሉት ምክትል ቢሮ ኅላፊው ምዝገባው መዳረሻነቱን ይበልጥ ያሳድገዋል ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!