
ደባርቅ: ሰኔ 10/2015 ዓ.ም (አሚኮ) 5ኛው ሀገር አቀፍ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርኃ ግብር “ነገን ዛሬ እንትከል” በሚል መሪ መልእክት መጀመሩ የሚታወስ ነው። በሰሜን ጎንደር ዞን ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርኃ ግብር ችግኝ በማፍላትና የመትከያ ቦታ በመለየት ዝግጅት እየተደረገ ነው።
በዞኑ ችግኝ እየፈላባቸው ከሚገኙ ቦታዎች መካከል በደባርቅ ወረዳ የሚገኘው “ራስ አምባ ችግኝ ጣቢያ” ተጠቃሽ ነው።የጣቢያው ተቆጣጣሪ በሬ አቡሐይ ካለፈው መስከረም ወር ጀምሮ የተለያዩ ችግኞችን በማፍላት ለተከላ ዝግጁ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ተናግረዋል። በጣቢያው ከ900 ሺህ በላይ የሳር ዝርያ፤ ከ490 ሺህ በላይ የደን ዛፎች እና ከ270 ሺህ በላይ የተለያዩ የፕላስቲክ ችግኞች ተፈልተው ለተከላ ዝግጁ መኾናቸውን አቶ በሬ አመላክተዋል።
የደባርቅ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አድምጠው እባቡ በወረዳው በሚገኙ 13 ሞዴል የችግኝ ጣቢያዎች ከ10 ሚሊዮን 500 ሺህ በላይ ችግኝ መፍላቱን ተናግረዋል።
የተዘጋጁት ችግኞች የሚተከሉበት ከ 1 ሺህ 250 በላይ ሄክታር የተከላ ቦታ መለየቱን የገለጹት የጽሕፈት ቤት ኀላፊው 105 ሄክታሩ በአንድ ጀንበር የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር የሚሸፈን ነው ብለዋል።በተለየው የተከላ ቦታ እስከአሁን ከ4 ሚሊዮን በላይ የችግኝ መትከያ ጉድጓድ ተቆፍሯልም ነው ያሉት።
የሰሜን ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ ኀላፊ ጌታቸው አዳነ በበኩላቸው ማኅበረሰቡ ችግኝ ተከላን ባሕል አድርጎታል ብለዋል። ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ከ57 ሚሊዮን በላይ ችግኝ ለማፍላት ታቅዶ የእቅዱን 75 በመቶ ወይም ከ43 ሚሊዮን በላይ ችግኝ ማፍላት መቻሉን አብራርተዋል።
አቶ ጌታቸው የተዘጋጀውን ችግኝ ለመትከል ከ7 ሺህ 600 ሄክታር በላይ የተከላ ቦታ ተዘጋጅቷል ብለዋል። ከዚህ ውስጥም በ46 ቀበሌዎች ከ1 ሺህ 600 በላይ ሄክታር ቦታ ላይ የአንድ ጀንበር ችግኝ ተከላ ለማከናወን እቅድ ተይዟልም ብለዋል። ከሰኔ 25/2015 ዓ.ም ጀምሮ የሣር ቁርጥራጭ ችግኝ የመትከል ሥራውም ይጀመራል ነው ያሉት።
ዞኑ ለአየር ንብረት ለውጥ እና ለአፈር መሸርሸር ተጋላጭ በመኾኑ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራ ትኩረት የምንሰጠው ተግባር ነው ያሉት አቶ ጌታቸው ለችግኝ ተከላ ትኩረት መስጠትና በየጊዜው የሚተከሉ ችግኞችን ከንክኪ ነጻ በማድረግና በመንከባከብ የጽድቀት መጠናቸውን ለማሻሻል እንሠራለን ብለዋል።
ዘጋቢ:-አድኖ ማርቆስ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!