
ባሕር ዳር: ሰኔ 10/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ሁሉን አውዳሚ ተመች በአማራ ክልል ተከስቷል። ሁሉን አውዳሚ ተመቹን መቆጣጠር ካልተቻለ በበልግ ዝናብ ሊገኝ የሚችለው ምርታማነት በእጅጉ ይጎዳዋል።
የሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ ወርቃለማሁ ኮስትሬ ዝናብ ቀድሞ በመጣሉ በዞኑ ቆላማ አካባቢዎች የአገዳ እህል ቀድሞ መዘራቱን ገልፀዋል። ቀድመው በዘሩ አካባቢዎች የአፍሪካ ተምች እና ሁሉን አውዳሚ የአሜሪካ ተምች የሚባሉት መከሰታቸውንም ተናግረዋል። የተከሰተውን ተምች በኬሚካል እና በባሕላዊ መንገድ የመቆጣጠር ሥራ እየተሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል። ከክልል ግብርና ቢሮ ጋር በመናበብ በፍጥነት የመቆጣጠር ሥራ እየተሠራ መሆኑንም ገልፀዋል። አርሶ አደሮች ማሳቸው ላይ ክትትል እንዲያደርጉም አሳስበዋል።
ተምች በብዛት ከተከሰተ ምርትና ምርታማነትን በእጅጉ እንደሚጎዳም አመላክተዋል። በዞኑ ተምችን ለመከላከል በቂ ስምሪት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል። የተከሰተውን ተመች መቆጣጠር ተችሏል ያሉት መምሪያ ኃላፊው ነገር ግን ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ ዳግም ሊከሰትበት የሚችለው እድል ሰፊ ነው ብለዋል። ባለፈው ዓመት ተመች ተከስቶ እንደነበርና አርሶ አደሮች ባላቸው ልምድ መቆጣጠር መቻላቸውንም አስታውሰዋል። ተምች በባሕሪው ከፍተኛ ክትትል ያስፈልገዋል ያሉት ኃላፊው አርሶ አደሮች የተምች ምልክት ሲያዩ ለግብርና ባለሙያዎች ማመልከት እንደሚገባቸውም ገልፀዋል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ ኃይለማርያም ከፍያለው (ዶ.ር) በክልሉ የተከሰተውን ሁሉን አውዳሚ ተምች አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ፤ ተምችን በፍጥነት እና በቁርጠኝነት መቆጣጠር ካልተቻለ የታየውን ምርታማነት ሙሉ ሊያቆምብን ይችላል ነው ያሉት። ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመሆን ኮምቦልቻ ላይ ባላው የፀረ ተባይ ቁጥጥር ማዕከል በቂ የሆነ ኬሚካል በማቅረብ ደቡብ ወሎና ሰሜን ሸዋ ያለውን ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠር ችለናል ብለዋል።
በሰሜን ወሎ የተከሰተውን ሕዝቡ እየተረባረበበት ነው ያሉት ኃላፊው በመቆጣጠር ላይ እንገኛለንም ብለዋል። ተመች በባሕሪው የሚዛመት በመሆኑ ተቆጣጠርን ብለን የምንዘናጋው ሳይሆን የየአካባቢው ነዋሪ ለግብርና በማመልከት፣ በማሳየት እና ለዘመቻው ተባባሪ በመሆን መሥራት ይጠበቅበታልም ብለዋል።
ተምቹን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የኬምካል አቅርቦት ችግር አለመኖሩንም አስታውቀዋል። ለምሥራቅ አማራ ኮምቦልቻ ማዕከል ላይ በበቂ ሁኔታ የኬሚካል አቅርቦት አስገብተናል ያሉት ኃላፊው ለዞኖችም በበቂ እያደረስን ነው ብለዋል። ተጨማሪ ግብዓት ካስፈለገም ማስገባት እንችላለን ነው ያሉት።
ዘጋቢ፦ ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!