ከክረምት ጋር ተያይዞ የሚፈጠረውን የኃይል መቆራረጥ ለመቀነስ እየሠራ መኾኑን የአማራ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት ገለጸ።

44

ባሕር ዳር: ሰኔ 10/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የክረምቱን ወቅት ተከትሎ በሚፈጠር ከባድ ነፋስ እና ዝናብ በተለይም በአሮጌ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመሮች እና ምሰሶዎች ላይ ጉዳት ይደርሳል። በኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች አቅራቢያ ዛፎች የሚኖሩ ከኾነ ደግሞ በነፋስ ምክንያት መነካካት ይፈጠርና ለመብራት መቆራረጥ ብሎም መጥፋት መንስዔ ይኾናሉ።

በባሕርዳር ከተማ ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች የክረምቱ መግቢያ ዝናብ ገና እንደጀመረ የመብራት መቆራረጡ እንደጨመረ ገልጸዋል። ዝናብ ጠብ እንዳለ ወዲያውኑ መብራት ይጠፋል ነው ያሉት።

አልፎ አልፎ መብራት ጠፍቶ ቆይቶ ሲመለስ ይዞት የሚመጣው ያልተመጣጠነ ኃይል በነዋሪዎች የኤሌክትሪክ መገልገያ ዕቃዎች ላይ ብልሽት መፍጠሩ ደግሞ ሌላው ጉዳት ነው።

ያረጁ የእንጨት ምሰሶዎች ተቀይረው፤ አሮጌ እና የተበጣጠሱ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ተጠግነው በቀላል ዝናብ የማይሸበር የኤሌክትሪክ አገልግሎት ማግኘት አለብን ሲሉም ነዋሪዎች ጠይቀዋል።

በአማራ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዲሰትሪቢውሽን ሲስተም ቴክኒካል ሳፖርት ኀላፊ አቶ ሽመላሽ ግርማው በክልሉ ያሉ ሰብስቴሽኖች አቅም ማነስና እርጅና ለመብራት መቆራረጥ አንዱ ምክንያት ነው ብለዋል።የመስመሮች ረዥም ርቀት መሄድ እና ገመዶቹ አሮጌ መኾናቸውም ሌላው የኀይል መቆራረጡ መንስዔ መኾኑን አንስተዋል።

አቶ ሽመላሽ ክረምቱን ተከትሎ የሚፈጠረውን የመብራት መቆራረጥ ችግር ለመፍታት በሁሉም ዲስትሪክቶች የቅድመ ጥገና ሥራ እየተከናወነ ስለመኾኑም ገልጸዋል፡፡

በክልሉ የኃይል መቆራረጥ ችግር ያለባቸውን አካባቢዎች በመለየት ክረምቱ ከመግባቱ በፊት ያረጁና ያዘመሙ የእንጨት ምሰሶዎችን የማስተካከልና የመቀየር፣የረገቡ የኃይል ማስተላለፊያ ሽቦዎችን የማስተካከል፣ የፕላስቲክ ስኒ ቅየራ እና በዛፍ የተዋጡ መስመሮችን ዛፉን የመቁረጥና የማጽዳት ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።

የትራንስፎርመር መቃጠልና በዚህ ምክንያት የሚከሰተውን የኃይል መቆራረጥ ለመቀነስም የዘመሙ ትራንስፎርመሮችን አቀማመጥ የማስተካከል፣ ዘይት የመቀየር፣ የመብረቅ መከላከያና ሌሎች የትራንስፎርመር ደህንነት መጠበቂያ መሳሪያዎች ገጠማ መከናወኑን ኀላፊው አንስተዋል።

በተከናወኑ ተግባራት 4500 ኪ.ሜ በላይ የመካከለኛ መስመር እና 3400 ኪ.ሜ በላይ የዝቅተኛ መስመር ጥገና መሠራቱንና ለ4600 ትራንስፎርመሮች ቅድመ ጥገና መደረጉን አቶ ሽመላሽ ተናግረዋል፡፡

አቶ ሽመላሽ በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች የሚገኙ የመንግሥት አስተዳድር አካላት እና ማኅበረሰቡ ለተቋሙ ሥራ ተባባሪ መኾን አለባቸው ብለዋል። በኤሌክትሪክ አስተላላፊ መስመሮች አቅራቢያ ዛፎችን ባለመትከል አጋርነትን ማሳየት ያስፈልጋልም ብለዋል። ከኤሌክትሪክ ሽቦዎች ጋር ንክኪ ሊፈጥሩ የሚችሉ ዛፎችን በመቁረጥ ተቋሙ አስተማማኝና ያልተቆራረጠ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ለመስጠት ለሚያደርገው ጥረት ሁሉም የድርሻውን ትብብር ማበርከት አለበት ሲሉም አቶ ሽመላሽ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የብልጽግናን እሴቶች በመላበስ ለሀገር አንድነት መሥራት ከብልጽግና ፓርቲ ተተኪ ሴት አመራሮች ይጠበቃል” የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚደንት አደም ፋራህ
Next article” በደቡብ ወሎና በሰሜን ሸዋ የተከሰተውን ተመች ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠር ችለናል” የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ ኃይለማርያም ከፍያለው ( ዶ.ር)