“የብልጽግናን እሴቶች በመላበስ ለሀገር አንድነት መሥራት ከብልጽግና ፓርቲ ተተኪ ሴት አመራሮች ይጠበቃል” የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚደንት አደም ፋራህ

93

አዳማ: ሰኔ 10/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአዳማ ለ10 ቀናት ሲሰጥ የቆየው የብልጽግና ፓርቲ የተተኪ ሴት አመራሮች ስልጠና ተጠናቋል።

ከተለያዩ የፌዴራልና የክልል ተቋማት እና ሴቶች ሊጎች ለተውጣጡ በብልጽግና ፓርቲ የአፈፃፀምና የፓርቲ ተሳትፎ ላይ የተሻሉ ለተባሉ ሴቶች በአዳማ ለ10 ቀናት ሲሰጥ የቆየው የተተኪ ሴት አመራሮች ስልጠና ማጠቃለያ መድረክ በገልማ አባገዳ አዳራሽ ተካሂዷል።

በተለያዩ የፓርቲው አሠራር፣ ራዕይ፣ የአመራር ክህሎቶችና ፅንሰ ሀሳቦች ስልጠና መሠጠቱን የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈጉባዔና በፓርቲው የሴቶች ሊግ ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ዘሐራ ዑመድ ገልጸዋል። ስልጠናውን የወሰዱ ተተኪ ሴት አመራሮች በተለያዩ ሴክተሮች ገብተው እንዲሠሩና የመሪነት ብቃታቸውን እንዲያረጋግጡም ጥሪ አቅርበዋል።

የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚደንት አደም ፋራህ ተተኪ ሴት አመራሮችን ለማፍራት የተዘጋጀው ስልጠና የብልጽግናን ዕይታዎች፣ ዕሴቶችና አስተሳሰቦችን ለማስረጽና ብቁ አመራር ለመፍጠር ወሳኝ መኾኑን አስረድተዋል።
ምክትል ፕሬዚደንቱ ፖለቲካዊ አካታችነት የድርጅቱ መርህ በመሆኑ እንዲሁም ለፓርቲው መጠናከር ጉልህ ሚና ስላለው ስልጠናው አስፈላጊ ስለመኾኑ አብራርተዋል።

አቶ አደም ፋራህ እንዳሉት በአመራር ውጤታማነት ላይ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት ሴቶች እኩል ዕድል ከተሰጣቸው የተሻለ ውጤት እንደሚያሳዩ ፣ቀውስ ሲከሰት ከመምራት አንጻር ያላቸው ብቃት የላቀ ነው። በተለይ ገዢው ፓርቲ በማኅበረሰቡ ያለውን ቅቡልነት ለማሳደግ እንደሚጠቅመው ነው ያብራሩት።

ሌላኛው ተተኪ ሴት አመራሮችን ለማፍራት የሚያስችለውን ስልጠና ለመስጠት አስፈላጊው ምክንያት ብለው የጠቀሱት ሴቶች በአመራርነት ያላቸው ቁጥር 20 በመቶ ብቻ በመኾኑና ከመድረክ ፍጆታ ባለፈ ትርጉም ባለው መልኩ ለውጥ ለማምጣት እንደኾነም ነው ያስረዱት።

እንደ ዓላማ የተያዙት መለየት፣ ማብቃትና መጠቀም ናቸው ያሉት አቶ አደም አቅም ያላቸውን መለየት፤ የሚያጋጥማቸውን ችግር መፍታት፤ ባላቸው አቅም ላይ ክፍተታቸውን በሚሞላ መልኩ ማብቃት፣ በቁጥር ከማሟላት የዘለለ አርዓያ እንዲኾኑ ማድረግና በቀጣይነት የድርሻቸውን የሚያበረክቱበትን ሁኔታ እንዲወጡ በሚመጥናቸው ቦታ መድቦ አቅማቸውን መጠቀም ያስፈልጋል ነው ያሉት።

ሴቶች በብዛት ወደ አመራርነት መምጣት አለባቸው ለዚህም አሠራር ተቀምጧል፤ የመጡት አመራሮችም ዕድሉን በአግባቡ መጠቀም አለባቸው ብለዋል።

ራስን ማብቃት፣ፓርቲውን የበለጠ ማወቅ፣ እሴቱን መላበስ ፣ፍጥነትና ፈጠራ በጣም አስፈላጊ እንደኾነም ነው ያስገነዘቡት። ሰልጣኞቹ ለሀገርና ለሕዝብ እንዲሠሩም የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንት በአፅንኦት ተናግረዋል።

ዘጋቢ፦ ድልነሳ መንግሥቴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የአቅመ ደካሞችን ቤት ማደስ መርሃ ግብር ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች በተገኙበት ተጀመረ።
Next articleከክረምት ጋር ተያይዞ የሚፈጠረውን የኃይል መቆራረጥ ለመቀነስ እየሠራ መኾኑን የአማራ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት ገለጸ።