
ባሕር ዳር: ሰኔ 10/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የክረምት የአቅመ ደካሞችን ቤት መሥራትና የጥገና ፕሮግራም የክልልና የፌዴራል ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች በተገኙበት በግሽ ዓባይ ክፍለ ከተማ ተጀምሯል።
በፕሮግራሙ የደቡብ ኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ርእሰ መሥተዳድር ርስቱ ይረዳው ተግኝተዋል።
በማስጀመሪያ ሥነሥርዓቱ ላይ የተገኙት ርእሰ መሥተዳድሩ “ከተባበርን የማንሻገረው ችግር የለም” ብለዋል።
የደቡብ ክልል መንግሥት የዛሬውን የአቅመደካሞች ቤት ጥገና እንዳስጀመረ ሁሉ የወዳጅነት አሻራችንን የምናሳይበት በባሕር ዳር ከተማ የተወሰኑ ቤቶችን ሠርተን ለችግረኞች እናስረክባለን” ሲሉም ቃል ገብተዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ባዬ አለባቸው በማስጀመሪያ ሥነሥርዓቱ ላይ እንደተናገሩት በክረምት መርሃግብሩ 50 የአቅመ ደካሞችን ቤት እንደሚጠግኑ ተናግረዋል።
” እየተባበርን የአቅመ ደካሞችን ችግር እንቀርፋለን” ብለዋል ምክትል ከንቲባው ባዬ አለባቸው።
ወጣቶችን፣ ባለሃብቶችንና ፈቃደኛ የበጎ አድራጎት ተሳታፊዎችን በማስተባበር የብዙ ችግረኛና አቅመደካማ የኀብረተሰብ ክፍሎችን ቤት እንጠግናለን፣ እንሠራለን ነው ያሉት። በተጨማሪም ፈቃደኛ ባለሃብቶች 30 የአቅመ ደካማ ቤቶችን ለመሥራት ቃል መግባታቸውንም ጠቅሰዋል።
ያረጀ ቤታቸው ጥገና የተደረገላቸው የከተማዋ ነዋሪዎችም ደስታቸውን ገልጸዋል። ያረጀው ቤቴ እያፈሰሰ ክረምት በመጣ ቁጥር እቸገር ነበር ያሉት የቀበሌ ሁለት ነዋሪ እማሆይ ነጠር መኮነን “ቤቴ እየተጠገነ ነው የሰላም እንቅልፍ ልተኛ ነውና ላደረጋችሁልኝ እርዳታ አመሠግናለሁ” ብለዋል። ፀሎቴ ሀገር ሰላም ይሁን ነው የሚሉት እማሆይ ነጠር ሀገር ሰላም ከኾነ ደካሞችን የሚዘነጋ ወገን እንደማይኖርም ተናግረዋል።
ሌላዋ የምትኖርበት የቀበሌ ቤት ጥገና የተደረገላት ወጣት ቅድስት ወርቁ ቤቷ በመታደሱ ደስታዋን ገልጻ ምሥጋናዋንም አቅርባለች። ከተማ አሥተዳደሩ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተባበረ በክረምትና በበጋ የአቅመ ደካሞችን ቤት በመሥራት ላይ መኾኑም ተገልጿል።
ዘጋቢ፦ ጋሻው አደመ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!