” የደሴ ወጣቶች የበጎ ፈቃድ ሥራዎች ለደሴዎች ኩራት፤ ለኢትዮጵያም ተምሳሌት ናቸው” ከተማ አሥተዳደሩ

51

ደሴ: ሰኔ 10/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የደሴ ከተማ አሥተዳደር የ2015 ዓ.ም የክረምት ወራት የወጣቶች በጎ ፈቃድ እቅድ ትውውቅ መድረክ እየተካሄደ ነው።

በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ ቁጥር 2 በሚል መሪ ሃሳብ የሚካሄደው የዘንድሮው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልጎሎት በደሴ ከተማ 80 ሺህ 614 ወጣቶችን በ13 የሥራ ዘርፎች እንደሚያሳትፍ ተገልጿል። የበጎ ፈቃድ ሥራው ከ80 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚገመት የከተማ አሥተዳደሩ ወጣትቶችና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ ሰይድ አራጋው ተናግረዋል።

በክረምቱ ወራት በሚሠራው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ79 ሺህ በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ እንደሚኾኑ አቶ ሰይድ ገልጸዋል።

“ለእኛ ለደሴዎች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አብሮን የተወለደና ያደገ ነባር ባሕላችን እንጂ አሁን የምንተገብረው አዲስ እሴት አይደለም ያሉት አቶ ሰይድ ፤ ከተራ ጎረቤት እርዳታ እስከ ትልልቅ የበጎ አድራጎት ሥራን በማሳያነት አንስተዋል።እነዚህ ተግባራት ለደሴ ኩራት፤ ለኢትዮጵያም ተምሳሌት ናቸው ብለዋል።

በዘንድሮው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚሰማሩ ዜጎች ቁጥር ከባለፈው ዓመት በ7 ሺህ ብልጫ እንዳለውም ተናግረዋል። በትውውቅ መድረኩ የደሴ ከተማ የተለያዩ ተቋማት የሥራ ኅላፊዎች፣የሃይማኖቶ አባቶች ፣የደሴ ከተማ በጎ ፈቃድ ማኅበራት አደረጃጀት አባላት ተገኝተዋል።

የደሴ ከተማ ብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካ ዘርፍ ምክትል ኀላፊ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለማኅበረሰቡ ጠቃሚ ተግባር የሚከወንበት የአገልግሎት ዘርፍ መኾኑን ተናግረዋል። የማኅበረሰቡን ባሕል፣ወግና እሴት በአግባቡ ለመረዳትና ለመተግበርም እድል የሚሰጥ በመኾኑ ሁሉም ሊረባረብ ይገባል ነው ያሉት።

የደሴ ከተማ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኀላፊ አለባቸው ሰይድ በበኩላቸው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ምንም አይነት ክፍያ የማይገኝበት ያለማንም ቀስቃሽና ጎትጓች በእራስ ተነሳሽነት የሚፈጸም ተግባር ነው ብለዋል፡፡ ይህ ተግባር ማንኛውንም ዜጋ የሚያሳትፍ ቢኾንም በዋናነት ወጣቶችን በስፋት የሚመለከት ተግባር ስለመኾኑም ገልጸዋል፡፡ ተግባሩ ማኅበራዊ ትስስርን፣ አንድነትንና ፍቅርን የበለጠ እንዲጠናከር ማድረግ ማስቻሉንም አቶ አለባቸው አንስተዋል።

የበጎ ፈቃድ ሥራው ተሳታፊ ወጣቶች ለአሚኮ እንዳሉት በክረምቱ ወራት የአረጋዊያንን ቤት በማደስ፣የችግኝ ተከላ በማከናወን፣ለጎርፍ የሚያጋልጡ ቦዮችን በማጽዳት እና በመጠገን እንዲሁም ሌሎች የበጎ ፈቃድ ሥራዎችን በመሥራት ያሳልፋሉ።

ዘጋቢ፦ አሊ ይመር

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበጤና መድኅን አገልግሎት አሰጣጥ የሚነሳውን የመድኃኒት ችግር ለመፍታት በክልሉ 124 ወረዳዎች ከግል ተቋማት ጋር ውል ይዘው እንዲሠሩ መደረጉን ጤና ቢሮ ገለጸ።
Next articleየባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የአቅመ ደካሞችን ቤት ማደስ መርሃ ግብር ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች በተገኙበት ተጀመረ።