
ባሕር ዳር: ሰኔ 10/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን አገልግሎት የማኅበረሰቡን በመንግሥት የጤና ተቋማት የመመርመር ባሕል እንዲያድግ ቢያደርግም የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር መኖሩን ያነጋገርናቸው የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ገልጸዋል፡፡
በባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ የኾኑት ወይዘሮ ፈንታነሽ አየነው እንዳሉት የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን ተጠቃሚ በመኾናቸው ሕመም በተሰማቸው ጊዜ ያለምንም የክፍያ ሥጋት ሕክምና እንዲያገኙ አድርጓቸዋል፡፡ አገልግሎቱ የማኅበረሰቡን በመንግሥት የጤና ተቋማት የመመርመር ባሕል እንዲያድግ ቢያደርግም የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር መኖሩን አንስተዋል፡፡
ከደራ ወረዳ ለሕክምና ወደ ፈለገሕይዎት አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል መምጣታቸውን የነገሩን ሌላኛው ግለሰብ፤ የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን አገልግሎት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚኖረው ማኅበረሰብ ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡ ይሁን እንጅ ከፍተኛ ዋጋ ያላቸው መድኃኒቶች ከመንግሥት የሕክምና ተቋማት እንደማይገኙና ከግል ተቋማት እንዲገዙ እየተደረገ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ ከገዙ በኋላ ደግሞ የገዙበትን ክፍያ ለመክፈል በተለያዩ መክንያቶች ማዘግየትና አልፎ አልፎም ያለመክፍል ችግር መኖሩን አንስተዋል፡፡
በአማራ ክልል ጤና ቢሮ የሃብት አሰባሰብ፣ አሥተዳደር እና አጋርነት ዳይሬክተር አዲሱ አበባው፤ የአገልግሎት አሰጣጥ፣ የግብዓት አቅርቦት በተለይም ደግሞ በመንግሥት የጤና ተቋማት የመድኃኒት እጥረት፣ የኪስ ትክ ክፍያ ያለመክፈል በመሰረታዊነት የሚነሱ ችግሮች ናቸው፡፡
በማኅበረሰቡ የሚነሳውን ችግር ለመፍታትም እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ በተለይም ደግሞ እያጋጠመ ያለውን የመድኃኒት አቅርቦት ችግር ለመፍታት ጤና ቢሮ ከመንግሥት ተቋማት በተጨማሪ ቀይ መስቀል መድኃኒት ቤቶች ላይ ውል ተወስዷል፤ እስከ አሁንም በዞኖች በሚገኙ አስር የቀይ መስቀል ቅርንጫፎች ላይ ውል ተይዞ አገልግሎት እየሰጡ መኾኑን ነው የገለጹት፡፡ ከዞኖች ባለፈ በወረዳዎችም ቅርንጫፍ እንዲከፍቱ እየተሠራ መኾኑን አንስተዋል፡፡
ከባለሙያዎች የሙያ ማኅበር ጋር በመነጋገር የግል የጤና ድርጅቶች ውል ተሰጥቶ አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጉንም ነው ያነሱት፡፡ በዚህም በክልሉ 124 ወረዳዎች ከግል ተቋማት ጋር ውል ይዘው ለማኅበረሰቡ አገልግሎት እየሰጡ መኾናቸውን ዳይሬክተሩ ነግረውናል፡፡ ዳይሬክተሩ እንዳሉት ወረዳዎች የራሳቸውን ፋርማሲ እንዲያቋቁሙም እየተሠራ ይገኛል፡፡ ለዚህ ደግሞ በኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር የደዋ ጨፋና ባቲ ወረዳዎች የማኅበረሰብ ፋርማሲ አቋቁመው አገልግሎት እየሰጡ መኾናቸውን ለአብነት አንስተዋል፡፡
የጤና ካምፓስ ያላቸው ዩኒቨርሲቲዎችም የማኅረሰብ አቀፍ ፋርማሲ እንዲያቋቁሙ እየተደረገ መኾኑንም ነግረውናል፡፡ ለዚህ ደግሞ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ እቴጌ ምንትዋብ ማኅበረሰብ አቀፍ ፋርማሲ ከፍቶ አገልግሎት በመስጠት ተጠቃሽ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ በቀጣይም ዩኒቨርሲቲዎችና የግል ተቋማት እንደ ‹‹ሲቲ ስካን››፣ የእንቅርት ምርመራ እና ሌሎች ትልልቅ ምርመራዎችን ለማኅበረሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ አገልግሎት እንዲሠጡ እየተሠራ ይገኛል፡፡
በክልሉ በሚገኙ ትልልቅ ከተሞች የሚመሩ የማኅበረሰብ አቀፍ ፋርማሲዎችን በማስፋፋት አገልግሎቱን ለመስጠት የሕግ ማእቀፍ እየተነዘጋጀ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡
ቢሮው በጤና መድኅን ተጠቃሚዎች የተነሳውን የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር ለመፍታት ከወሰደው መፍትሄ ባለፈ ችግር ፈጥረው በተገኙ ተቋማት ላይም ሕጋዊ እርምጃ መወሰዱን ዳይሬክተሩ ነግረውናል፡፡ በዚሕም በባሕር ዳር ከተማ በመድኃኒት ሽያጭ ያልተገባ ድርጊት ፈጽመው በተገኙ የመድኃኒት አከፋፋይ ተቋማት ላይ ቢሮው ከክልሉ የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን፣ ከፍትሕ፣ ከገቢዎች፣ ከገንዘብ ቢሮ፣ ከግል ጤና ተቋማት ማኅበር እና ከሌሎች ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመቀናጀት እስከ ሁለት ዓመት ድረስ እንዲታገዱ መደረጉን አንስተዋል፡፡ በወረዳዎችም ከሕጋዊ ተቋማት ያልተገዛ መድኃኒት ሲሸጡ የተገኙ የግል አገልግሎት ሰጭ ተቋማትም ውላቸው መቋረጡን ገልጸዋል፡፡
የማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድኅን የተበጣጠሰ ክፍያን በማስቀረት እንደ ሀገር ወጥ የኾነ ሥርዓትን ለመፍጠር የሚያስችል አዋጅ በሀገር አቀፍ ደረጃ መውጣቱን ነው የገለጹት፡፡
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!