
ባሕር ዳር: ሰኔ 10/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕርዳር ስልጠና ሲወስዱ የቆዩ የብልፅግና ፓርቲ መሪዎች በዘንዘልማ ችግኝ ተክለዋል። በችግኝ ተከላው ላይ መልእክት ያስተላለፉት የደቡብ ክልል ርእሰ መስተዳድር እርስቱ ይርዳው፤ ወደ አማራ ክልል ስንመጣ ብዙ ጥበብ ቀስመን ነው የምንሄደው ብለዋል።
የአማራ ሕዝብ የጥበብ ምንጭ መሆኑን አይተናል። የጥበብ ምንጭነቱ ተቀድቶ የሚያልቅ አይደለም ነው ያሉት። የአማራ ሕዝብ በአንድነት በመውጣት ሀገር በመጠበቅ እና በሌሎች ተግባራት አርዓያነት ያለው ተግባር የሚፈፅም መሆኑንም ገልፀዋል። ለአማራ ሕዝብም ምስጋና ይገባዋል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ ታላቅ ሥራ ጀምራለች ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ፤ በአረንጓዴ ዐሻራ ለዓለም መልስ የሚሰጥ ተግባር መሥራቷንም ገልፀዋል። ባለፉት ዓመታት በጀመረቻቸው ሥራዎች የአየር ንብረት ለውጥን ለመታገል አወንታዊ አስተዋጽኦ ማበረከቷንም ገልፀዋል። ለአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ከሚፈጥሩ ሀገራት የበለጠ ችግሩን ለመከላከል እየሠራች ነው ብለዋል። ለአየር ንብረት መዛባት አስተዋጽኦ ባይኖራትም ለመፍትሔው ከግንባር ቀደሞቹ ናትም ብለዋል።
ኢትዮጵያ ለዓለም ምሳሌ የሆነ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር እያካሄደች መሆኗንም ገልፀዋል። ሥራው ዓለም አቀፍ አድናቆትን ቢያተርፍም ያልተጠናቀቀ ወደፊት ብዙ ሥራዎች የሚያስፈልጉት መሆኑንም አስታውቀዋል። ኢትዮጵያ በሃብቷ መጠቀም አለባት ያሉት አቶ እርስቱ ሕዝቡ ካለው ሃብት በመጠቀም የተፈጥሮ አደጋን መካከል አለበትም ብለዋል።
የሕዳሴ ግድብ ግንባታ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል እና የደን ጭፍጨፋን ለመከላከል አይነተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውም ገልፀዋል። ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድቡን ግንባታ ሁሉም ሀገራት ሊያበረታቱት የሚገባ መሆኑንም አንስተዋል። በሀገር አቀፍ ደረጃ የተተከለው ችግኝ 83 በመቶ የፅድቀት መጠን እንዳለውም ገልፀዋል።
የተራቆተች ሳይሆን ለምለም የሆነች ኢትዮጵያን ለትወልድ ማስረከብ አለብንም ብለዋል። ዓለምን እየፈተነው ያለውን የአየር ንብረት ለመፍታት የችግኝ ተከላው አማራጭ የሌለው መፍትሔ መሆኑንም ገልፀዋል። ባለፉት ቀናት ባደረጉት ምክክር ሀገርን ሊያንፁ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውንም አስታውቀዋል። ከምክክሩ ባለፈ የአንድነት እና ማሳያ በሆነው ዐሻራቸውን በአንድ ላይ ማሳረፋቸውንም ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦ ታርቆ ክንዴ