“ሥልጠናው የአማራን ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎች ለሌሎች ለማስረዳት እድል ፈጥሯል” ዶክተር ጋሻው አወቀ

89

ባሕር ዳር: ሰኔ 09/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ብልጽግና ፓርቲ ለአማራ ክልል ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች ሲሰጥ የቆየውን ስልጠና በስኬት ማጠናቀቁን አስታውቋል፡፡ ላለፉት አራት ቀናት በክልሉ ርእሰ ከተማ ባሕር ዳር ሲሰጥ የቆየው ድርጅታዊ ሥልጠና ውጤታማ እና የተሳካ እንደነበር የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ የአደረጃጀት ዘርፍ ኅላፊ ጋሻው አወቀ (ዶ.ር) ገልጸዋል፡፡ በክልሉ በየደረጃው የሚገኙ 1 ሺህ 150 አመራሮች በሥልጠናው መሳተፋቸው ተጠቁሟል፡፡

ሥልጠናው በሀገሪቱ እና በክልሉ ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ፣ ማህበራዊ እና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የመከረ መድረክ እንደነበር ያነሱት ዶክተር ጋሻው የሃሳብ የበላይነት የታየበት፣ ዴሞክራሲያዊ እና አሳታፊ ነበር ብለዋል፡፡ ሥልጠናዊ መድረኩ በተለይም የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት እና የሌሎች ክልሎች አመራሮች የመሩት በመሆኑ እርስ በእርስ ለመቀራረብ እና ለመተዋወቅ እድል የፈጠረ ነበር ብለዋል፡፡

የአማራ ሕዝብ በሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደት ጉልህ ሚና የነበረው ሕዝብ ቢሆንም በተሳሳቱ ትርክቶች በርካቶች በተሳሳተ መንገድ እንዲረዱት አድርጓል፡፡

በዚህ ሥልጠናዊ ውይይት ከሌሎች ክልሎች የመጡ የፓርቲው የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት የክልሉን ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎች እንዲረዱ ያገዘ ነበር ያሉት ዶክተር ጋሻው “ሥልጠናው የአማራን ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎች ለሌሎች ለማስረዳት እድል ፈጥሯል” ነው ያሉት፡፡

ከዚህ ሥልጠናዊ መድረክ ቀድሞ የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ ተሰብስቦ ከተወያየ በኋላ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል፡፡ የድርጅቱን የቀጣይ ጊዜያት አቅጣጫዎች በሚፈለገው መንገድ መሬት ለማስነካት ሥልጠናዊ ውይይቱ ያስፈልግ ነበር ያሉት ዶክተር ጋሻው ተቀራራቢ የመፈጸም አቅም ለመገንባት በሚያስችል መልኩ በስኬት ተጠናቋል ብለዋል፡፡

ዶክተር ጋሻው ውስጣዊ አንድነትን ማጠናከር የውጭ ተጋላጭነትን ለመቀነስ ይጠቅማል የሚለው ሃሳብ በሥልጠናዊ ውይይቱ የጋራ አቋም የተያዘበት መሆኑንም አንስተዋል፡፡ የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት የመሩት ሥልጠናዊ ውይይት መሆኑ አንዱ ሌላውን እንዲያደምጥ እና እንዲረዳ የሚያግዝ ሆኗል ተብሏል፡፡

የአማራ ክልል አመራሮች ወደ ሌሎች ክልሎች ሄደው ያወያዩበት እና የሌሎች ክልሎች አመራሮችም ወደ አማራ ክልል መጥተው ማስልጠናቸው እና መሰልጠናቸው ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር እድል የፈጠረ እንደነበርም ተነስቷል፡፡
በቀጣይም ውስጣዊ አንድነትን ከማጠናከር ባሻገር ግንኙነቱን የበለጠ ለማጠናከር እና አንዱ ሌላውን በውል እንዲረዳ ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ ተምረናል ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ዘመኑን የሚመጥን አሠራር እየዘረጋን ነው” የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ
Next article“የተራቆተች ሳይሆን ለምለም የሆነች ኢትዮጵያን ለትውልድ ማስረከብ አለብን” የደቡብ ክልል ርእሰ መስተዳደር እርስቱ ይርዳው