
ባሕር ዳር: ሰኔ 09/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በዘመናዊው ዓለም ቴክኖሎጂ ውስብስብ እና አድካሚ ሥራን ቀላል፣ ቀልጣፋና ውጤታማ በማድረግ ረገድ የማይተካ ሚና እየተጫወተ ነው። ቴክኖሎጂ የዘመኑ መፎካከሪያም መወዳደሪያም ኾኗል።
በየዘርፉ ሥራንና አሠራርን ያቀለሉ፣ሥራንም በአግባቡ ለመምራትና ለማሥተዳደር የሚያስችሉ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች የሰውን ልጅ ሥራና የአኗኗር ዘይቤ እያቀለሉ ይገኛሉ። ኢትዮጵያም ለዲጂታል ቴክኖሎጂ ትኩረት በመስጠት ላይ ስለመኾኗ እየተነገረ ነው።
በአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ውስብስብ የኾነውን የገቢ ግብር አሰባሰብ ሥርዓት በልኩ ለመምራት አስቻይ ተግባር መጀመሩ ተገልጿል።
ግብርን በዲጂታል አሠራር ለመክፈል፣ ሰነድን በአግባቡ ለመያዝ፣ መረጃን ለማሰራጨትና ለማሥተዳደር የሚያስችል ዘመኑ የፈቀደውን የዲጂታል አሠራር ሥርዓት ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ነው ተብሏል።
የክልሉ ገቢዎች ቢሮ የግብር፣ ትምህርትና ኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር አግማስ ጫኔ ለአሚኮ ኦንላይን ሚዲያ እንደተናገሩት ቢሮው “ዘመኑ የደረሰበትን ደረጃ የሚመጥን አሠራር እየዘረጋ ነው” በነበረው አሠራር የገቢ ተቋሙን በውጤታማነት ማሥተዳደር የማይቻል ይኾናል የሚሉት ዳይሬክተሩ ዲጂታል የግብር አሰባሰብ፣ የደንበኞች መረጃና የሰነድ አያያዝ ላይ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመሥጠት ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ ነው ብለዋል።
አቶ አግማስ እንደሚሉት ለገቢዎች ቢሮ “ሰነድ ገንዘብ ነው”፣ እናም በሰነድ ላይ በሥነ-ምግባር ጉድለት፣ በአደጋና መሰል ሁኔታዎች የሚደርስን ጥፋት ለማስቀረት በክልሉ ገቢዎች ቢሮና ከገቢዎች ሚኒስቴር የበለጸጉ ሶፍትዌሮችን በአግባቡ ለመጠቀም እየተሠራ ነው ብለዋል።
ቢሮው በበለጸገ ሶፍትዌር የግብር ከፋዩን ማኅደር በዲጂታል በማደራጀት ላይ ነው ተብሏል። ዲጂታል የግብር አከፋፈል ትግበራውን በክልሉ በሁሉም ሪጂኦፖሊታንት ከተሞች ለመተግበር ጥናት ተደርጓል ነው የተባለው።
ባለፉት 10 ወራትም ከ148 ሺህ 400 በላይ ግብር ከፋዮችን፣ ከ20 ሺህ 900 በላይ የመሬት ሊዝ መረጃን፣ ከ4 ሺህ 500 በላይ ድርጅቶች የሥራ ግብር መረጃን በዘመናዊ መንገድ ተደራጅቶ ወደ ሲስተም ማስገባት እንደተቻለ ነው የተነገረው።
ግብር ከፋዮች የገቢ ተቋሙን ሲስተም በመጠቀም የሚመለከታቸውን የግብር ዓይነቶች የማስታወቅ፣ክፍያን የመክፈልና የከፈሉበትን ደረሰኝ ባሉበት ኾነው ማግኘትን የሚያስችል የኤሌክትሮኒክስ ታክስ አከፋፈል በባሕር ዳር ከተማ በተመረጡ ግብር ከፋዮች ላይ መተግበር ተጀምሯል ብለዋል ዳይሬክተሩ።
ሌላው የኔት ወርክ ዝርጋታ ተደራሽነት በተረጋገጠበት አካባቢ የመረጃ ልውውጡን ዲጂታላይዝድ የማድረግ ሥራው 98 በመቶ ማድረስ መቻሉም ተገልጿል።
ግብር ከፋዩ ማኅበረሰብ ግብሩን በዲጂታል እንዲከፍል እና ሌሎችንም ሥራ የሚያዘምኑ የአሠራር ሥርዓትን በመዘርጋት ረገድ ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ እየተሠራ ነው ብለዋል።
ዘጋቢ:-ጋሻው አደመ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!