ጃፓን በአማራ እና ትግራይ ክልሎች ለሚደረገው የትምህርት ቤት እና የንጹህ መጠጥ ውኃ መልሶ ማልማት ፕሮጀክት 8 ነጥብ 1 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አደረገች።

56

አዲስ አበባ: ሰኔ 09/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የማኅበራዊ መሰረተ ልማትን በአማራ እና ትግራይ ክልሎች ማሻሻል ፕሮጀክት በዩኒሴፍ ኢትዮጵያ እና በጃፓን ዓለም አቀፍ ተራድኦ ኤጀንሲ (ጃይካ) በኩል ይተገበራል።

ይህን የመልሶ ግንባታ ሥራ ለማከናወን የጃፓን ኢምባሲ ከዩኒሴፍ እና ጃይካ ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል።

በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ኢቶ ታካኮ “ዛሬ የጋራ ስምምነት ተፈራርመናል ይህም 8 ነጥብ 1 ሚሊዮን ዶላር ነው” ብለዋል። ድጋፉ የሚውለው በምሥራቅ አማራ እና በትግራይ የተጎዱ ትምህርት ቤቶችን እና የንፁህ መጠጥ ውኃ አቅርቦትን ለማሟላት ነው።

አምባሳደሯ እንዳሉት በአማራ እና በትግራይ ክልል በርካታ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ናቸው። አሁን የተደረገው ድጋፍ ከትምህርት ገበታ ውጭ የኾኑ ታዳጊዎችን ችግር ለመቅረፍ እንደኾነም አስረድተዋል፡፡ በሚሠራው ሥራም ተማሪዎች ወደ ትምህርት ሲመለሱ የተሻለ ትምህርት እና የንጹህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት ማግኘት እንዲችሉ ያደርጋል።

የተሻለ መስረተ ልማት መኖር በሕፃናቱ ህይዎት ላይ ለውጥ ያመጣል ይህን ለማድረግም ድጋፉ ከጃፓን ሕዝብ ለኢትዮጵያ የተበረከተ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ የዩኒሴፍ ተወካይ አቡበከር ካምፖ (ዶ.ር) ይህ ድጋፍ በትምህርት ቤቶች ንጽህናን ለመጠበቅ፣ የንጹህ መጠጥ ውኃ ለማግኘት እና የትምህርት መሰረተ ልማትን ለማሟላት የሚደረግ ጥረትን በእጅጉ የሚደግፍ ነው ብለዋል።
በሁለቱም ክልሎች ትምህርት ቤቶች ሙሉ ለሙሉ፣ አልያም በከፊል ወድመዋል ያሉት በኢትዮጵያ የዩኒሴፍ ተወካይ ይህንን ችግር ለመፍታት ዩኒሴፍ ጥረቱን አጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት፡፡ የዛሬው ድጋፍም ለዚህ ወሳኝ አቅም እንደሚፈጥር አስገንዝበዋል።

ጃይካ በበኩሉ “እኛ በዚህ ስንሳተፍ ዋና ተግባራችን የቴክኒክ እና የሙያ ድጋፍ ከማድረግ ባለፈ ረጅም ጊዜ የቆየውን የሁለቱ ሀገራት የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር ነው” ብሏል።

የትምህርት ሚኒስቴር ለተደረገው ድጋፍ አመስግኖ በእነዚህ አካባቢዎች ከተጎዱ 1ሺህ 335 ትምህርት ቤቶች ውስጥ አሁን ላይ 24 ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት የሚያበቃ ገንዘብ ብቻ መገኘቱን የተናገሩት በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የስትራቴጅክ ጉዳዪች ዳይሬክተር መዝገቡ ቢያዝን ናቸው፡፡ የጃፓን መንግሥት ላደረገው ድጋፍም አመሥግነዋል።

ዘጋቢ፡- አንዱዓለም መናን

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleቡናን ጨምሮ ሌሎች ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ያላቸው የቆላ እና የደጋ ፍራፍሬ ችግኞችን ለተከላ ማዘጋጀቱን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡
Next article“ዘመኑን የሚመጥን አሠራር እየዘረጋን ነው” የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ